1795612659125

በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሙስና ትስስር ያለባቸው ተቋማትና ዘርፎች ይፋ ሆኑ፤ የኢኮኖሚና የደኅንነት ስጋቶችም ተጠቆሙ

​የፌዴራል የሥነ-ምግባር እና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን 23ኛውን ዓለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ቀን አስመልክቶ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ በኢትዮጵያ ከቀበሌ እስከ ከፍተኛ የመንግሥት መዋቅሮች ድረስ በስፋት ሙስና የሚፈጸምባቸውን ተቋማትና ዘርፎች ይፋ አድርጓል።

በመግለጫው ኢሚግሬሽን፣ ጉምሩክ፣ ፍርድ ቤቶች እና ሪል እስቴት በቀዳሚነት የተጠቀሱ ሲሆን፣ የተደራጀው የሙስና ሰንሰለት በኢኮኖሚ፣ በህግ የበላይነት እና በብሔራዊ ደኅንነት ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑ ተመላክቷል።

​ኮሚሽኑ እንዳስታወቀው ወሳኝ ኩነት፣ ኢሚግሬሽን፣ ጉምሩክ፣ ፖሊስ ጣቢያዎች፣ ፍርድ ቤቶች፣ የፍተሻ ኬላዎች እንዲሁም የማዕድን፣ የመሬት አሰጣጥ፣ የሪል እስቴት እና የኮንስትራክሽን ዘርፎች ከፍተኛ የሙስና ትስስር ያለባቸው ተቋማት ናቸው።

​በእነዚህ ተቋማትና ዘርፎች ውስጥ በስፋት ከሚፈጸሙ ድርጊቶች መካከል ​ሐሰተኛ ሰነዶችና የሕግ ሂደት ማዛባት ተጠቅሷል።

ለሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር የሚውሉ ሐሰተኛ ፓስፖርትና መታወቂያ ማዘጋጀት፣ የፍርድ ወይም የምርመራ መዝገብ ማጥፋት፣ ምስክሮችን ማስፈራራት እና ወንጀለኞችን ያለበቂ ዋስትና መልቀቅ ይገኙበታል።

​በባንክ፣ በጉምሩክና በሪል እስቴት ዘርፎች ባሉ አካላት መመሳጠር ምክንያት በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር በሕገ-ወጥ መንገድ ከሀገር እንደሚወጣና ለመድኃኒትና ለነዳጅ የሚውል የውጭ ምንዛሪ እያሳጣ መሆኑ ተገልጿል።

በተጨማሪም በወንጀል የተገኘ ገንዘብን ሕጋዊ ለማስመሰል የከተማ መሬቶችንና ሕንፃዎችን በተጋነነ ዋጋ በመግዛት የቤት ዋጋ ንረትንና የኑሮ ውድነትን የማባባስ ተግባር እየተፈጸመ መሆኑ ተመላክቷል።

​የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ በፍተሻ ጣቢያዎች፡ በሞጆ፣ በቶጎ ውጫሌ፣ በሞያሌ፣ በመተማ፣ በጅግጅጋና በጋላፊ የፍተሻ ጣቢያዎች በሚፈጸም ሙስና ወርቅና የከበሩ ማዕድናት በኮንትሮባንድ ወደ ጎረቤት ሀገራት እየሸሹ መሆኑ ተጠቁሟል።

​የተደራጀው የሙስና ሰንሰለት የመንግሥትን የልማት በጀት ከማዳከም ባለፈ ሕጋዊ ነጋዴዎችን ከገበያ እያስወጣ መሆኑን ኮሚሽኑ አስገንዝቧል።

ከዚህም በላይ ድንበሮችን ለጦር መሣሪያ ዝውውርና ለአሸባሪዎች ክፍት በማድረግ ብሔራዊ ደኅንነትን አደጋ ላይ እየጣለ እንደሚገኝ አሳስቧል።

​ኮሚሽኑ ዜጎች ጉዳያቸውን ለማስፈጸም ጉቦ በመስጠት ሕጋዊ መብታቸውን በገንዘባቸው እየገዙ መሆኑን እንዲገነዘቡ በማሳሰብ፣ «ስውር ትስስሮችን በማጋለጥ የሙስና ወለድ ወንጀሎችን ሰንሰለት እንበጥስ» በሚለው መሪ ቃል ሙስናን በጋራ እንዲታገሉ ጥሪ አቅርቧል።