በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቡርጂ ዞን ሶያማ ዙሪያ ወረዳ እና በኦሮሚያ ክልል ሱሮ ባርጉዳ ወረዳ አዋሳኝ አካባቢዎች ተፈጥሮ የነበረውን የጸጥታ ቀውስ ተከትሎ የአካባቢውን ሰላም ለማጽናት እና የተዘረፉ ንብረቶችን ለማስመለስ ያለመ የጋራ የሰላም ኮንፈረንስ መድረክ ህዳር 16 ቀን 2019 ዓ.ም በቡርጂ ዞን ሶያማ ተካሂዷል።
ይህ መድረክ የተዘጋጀው ከአንድ ወር በፊት በሶያማ ዙሪያ ወረዳ ነደሌ ቀበሌ በእርሻ ማሳቸው ላይ ሲሰሩ በነበሩ 7 ንጹሃን አርሶ አደሮች ላይ በተፈጸመ ጥቃት ህይወታቸው ካለፈ እና በርካታ ከብቶችና ንብረቶች ከተዘረፉ በኋላ የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ ነው።
WT Media ቀደም ሲል ጥቅምት 19 ቀን 2019 ዓ.ም (እ.ኤ.አ. ጥቅምት 29 ቀን 2026) እንደዘገበው ጥቅምት 12 ቀን 2019 ዓ.ም በነደሌ ቀበሌ በእርሻ ማሳቸው ላይ በሰላም ሲሰሩ በነበሩ አርሶ አደሮች ላይ በተፈጸመ ጥቃት 7 አርሶ አደሮች ሲገደሉ በርካታ ከብቶችም በአደባባይ ተዘርፈው ነበር። በወቅቱ የቡርጂ ዞን አስተዳደር ባወጣው መግለጫ ጥቃቱ ከምዕራብ ጉጂ በኩል በመጡ ጽንፈኛ አካላት የተፈጸመ መሆኑን ጠቅሶ፣ ወንጀለኞች ለህግ እንዲቀርቡ እና የአጎራባች አስተዳደር አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርቦ ነበር።

የአካባቢው ነዋሪዎችም በተደጋጋሚ በእርሻ ማሳዎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች እንዲቆሙ፣ መንግስት ከቃላት መግለጫ ባለፈ የዜጎችን ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲያስከብር እና አጥፊዎችን ለህግ እንዲያቀርብ ሲጠይቁ ቆይተዋል።
የቡርጂ ዞን የመንግስት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ዛሬ ህዳር 16 ቀን 2019 ዓ.ም (እ.ኤ.አ. ህዳር 25 ቀን 2026) ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት በሶያማ ዙሪያ ወረዳ እና በሱሮ ባርጉዳ ወረዳ አመራሮች፣ በጥምር ኮሚቴዎች እና በሀገር ሽማግሌዎች መካከል በተደረገው ውይይት የሚከተሉት ዋና ዋና ነጥቦች ተነስተዋል።
የሶያማ ዙሪያ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ያዕቆብ ቤጦ ግጭት በሚፈጠርበት የመሬት ጉዳይ ዙሪያ በመግባባት ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ህዝቡ መረጋጋት እንዳለበት አሳስበዋል። አክለውም የጥይት ድምጽ እንዳይሰማና የተወሰዱ ንብረቶች እንዲመለሱ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የቡርጂ ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ማቴዎስ ጎልጃ ከነደሌ ቀበሌ አካባቢ እና ከሱሮ ባርጉዳ በኩል የተወሰዱ ከብቶች ጉዳይ ለጥምር ኮሚቴው በጥልቀት ቀርቦ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት የሚሰራበት ቀጣይ አቅጣጫ መሆኑን አመላክተዋል።

የሱሮ ባርጉዳ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ደስታ ሻዋሌ ሰሞኑን በያቤሎ ከተማ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ውይይቶች መጀመራቸውን ገልጸው፣ በሱሮ ባርጉዳ መንገድ የመኪና እንቅስቃሴ እንዲጀምርና የተወሰዱ ንብረቶችን የማስመለስ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል። የወረዳው የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኤልያስ ማቴዎስም መንግስት ከጥምር ኮሚቴዎችና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር በመሆን ለሰላም ጸር የሆኑ ክስተቶችን እግር በእግር እየተከታተለ እንደሚያርም ገልጸዋል።
በመድረኩ የተሳተፉ የሀገር ሽማግሌዎችና የጥምር ኮሚቴ አባላት በምክክር በተሰራው ስራ ሊፈጠር የነበረውን ተጨማሪ ግጭት ማስቆም መቻሉን ጠቅሰው የውስጥ መተዳደሪያ ደንብ አውጥተው እየተመሩበት መሆኑን ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ችግሩ ከስሩ እንዲፈታ ሌቦችንና አጥፊዎችን የማጋለጥ እና ለህግ የማቅረብ ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ መንግስትም በጸረ-ሰላም ኃይሎች ላይ ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ አሳስበዋል።
በሁለቱም ዞኖች በሚገኙ የሀገር ሽማግሌዎች የጋራ የመመራረቅ ስነ-ስርዓት የተጠናቀቀው ይህ መድረክ በቃል የሚገቡ የሰላም ስምምነቶች ወደ ተግባር ተቀይረው የሟቾች ቤተሰቦች ፍትህ እንዲያገኙ፣ የተዘረፉ ንብረቶች እንዲመለሱ እና በመሬት ይዞታ ዙሪያ ያሉ አለመግባባቶች ዘላቂ እልባት እንዲያገኙ የአካባቢው ማህበረሰብ በትኩረት የሚጠብቀው ጉዳይ ሆኗል።