የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ ወንድማገኝ ደግፌ

“ፈቃድ ሳይኖራቸው ፎቅ የሚያበቅሉና የኢንቨስትመንት መሬት በሚወስዱ ላይ እርምጃ እንወስዳለን” - የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ ወንድማገኝ ደግፌ

የንብረት ግብር አዋጅ፣ የአካውንት ኦዲት እና የንግድ ፈቃድ የሌላቸውን የኢንቨስትመንትና የህንፃ እንቅስቃሴዎች የመከታተል እርምጃ ተጠቆመ

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ ወንድማገኝ ደግፌ በመድረክ ባደረጉት ንግግር፤ በከተሞች ውስጥ ምንም ዓይነት የደረጃ ፈቃድም ሆነ የጸና የንግድ ፈቃድ ሳይኖራቸው ፎቅ የሚያበቅሉ፣ የኢንቨስትመንት ቦታ የሚወስዱና ምንጩ ያልታወቀ ሀብት የሚያፈሩ አካላት ላይ የአካውንት ኦዲትና የግብር ክትትል ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

የንብረት ግብር አዋጅ መምጣቱን ተከትሎ የንግድ ዘርፍም ሆነ ፈቃድ ሳይኖራቸው ሀብት ያፈሩ ሰዎች የገንዘብ ምንጭ በአካውንት ኦዲት እንደሚጣራ ተጠቁሟል። በኢትዮጵያ ካሉ 32 ባንኮች (የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የልማት ባንክን ጨምሮ) ጋር በተያያዘ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እንደሚመረመሩ ተገልጿል።

ሕጋዊ ነጋዴዎች ግብራቸውን በሕግ አግባብ እንዲከፍሉ ክትትልና ኦዲት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፣ ፈቃድ ሳይኖራቸው ደላላ ሆነው የሚንቀሳቀሱና የንግድ እንቅስቃሴ ሳይኖራቸው ሕንፃ የሚያበቅሉ አካላት አካውንታቸው ኦዲት ተደርጎ ታክስ የሚከፍሉበት ሥርዓት እየተዘረጋ መሆኑን ገልጸዋል። በጊዜው ፈቃድ እንዲያወጡም መክረዋል።

አስተዳደርና ዞን አመራሮች የንግድ ፈቃድ የሌላቸው አካላት እንዴት የኢንቨስትመንት ቦታና መሬት ሊያገኙ እንደቻሉ በጥልቀት ማጣራትና ተገቢውን ውሳኔ መስጠት እንዳለባቸው አሳስበው፣ ቀጣይ ተጣርቶ ወደ መንግሥት ገቢ ሊሆን የሚችልበት አሠራርና ሥርዓት እየተዘረጋ መሆኑን ተናግረዋል።