በቅርቡ በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ የዎላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ እጩ ሆኖ የተወዳደረው እና በዎላይታ ዞን በቦዲቲ ከተማ የትምህርት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ተደርጎ የተሾመው አርቲስት ቡንጌ ቡሩንጄ በፌስቡክ ገጹ ያስተላለፈው ጠንካራ መልዕክትና ተከትሎት የቀረበው የማስተካከያ መልዕክት በማህበረሰቡ ዘንድ ሰፊ ውይይት ቀስቅሷል።
መልዕክቱ የማህበራዊ እኩልነት፣ የህጻናት መብት እና በማህበረሰብ ውስጥ ስለሚስተዋሉ መገለሎችና አለመግባባቶች ያተኮረ WT Media ለመታዘብ ችሏል።
አርቲስት ቡንጌ ቡሩንጄ በመጀመሪያው መልዕክቱ በማህበረሰቡ ውስጥ ያሉ አንዳንድ መገለሎችንና በህጻናት ላይ የሚደርሰውን የጉልበት ብዝበዛና ስደት በጠንካራ ቃላት ተችቷል። በመልዕክቱም የውስጥም ሆነ የአጎራባች ማህበረሰቦች መብት፣ ክብር እና እኩልነት እንዲረጋገጥ አሳስቧል።

ይሁን እንጂ ከዚህ መልዕክት በኋላ በማግስቱ በድጋሚ ባስተላለፈው ሌላ መልዕክት፤ «ችግር ተፈጥሮ ነበር። በክቡር ከንቲባችንና አስተባባሪ አካላት አማካኝነት ችግራችን ተፈቷል። አሁን በሠላም ወደ ሥራ ገብተናል። ስለረበሽናችሁ ይቅርታ እንጠይቃለን» ሲል አስታውቋል።
ከህይወት ታሪኩና ከቀድሞ መረጃዎች ለመረዳት እንደሚቻለው ቡንጌ ቡሩንጄ በትምህርትም ሆነ በጥበብ ዘርፍ የራሱን አሻራ ያሳረፈ ግለሰብ ነው።
በ1993 ዓ.ም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን በመቀላቀል የኢኮኖሚክስ ትምህርቱን በከፍተኛ ውጤት ያጠናቀቀ ሲሆን በጥበብ ዓለምም «ካዎ ጦና» እና የኦሞቲክ ቤተሰብ አርቲስቶችን ያሳተፈ «ሃሎ ሳውዝ ኢትዮጵያ» የተሰኙ አልበሞችን ጨምሮ የተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮችን የሚዳስሱ ስኬታማ ስራዎችን አቅርቧል።
ከእነዚህም መካከል በደቡብ ኦሞ ዳሰነች ወረዳ በጎርፍ አደጋ ህይወታቸውን ላጡ ዜጎች የተሰራው «ታናሞ» እና ለአቶ ፍሬው አልታዬ የተሰራው «ጃላ ጋራንጌ» እንዲሁም የሰዎችን ሰብአዊ ክብር የሚነኩ እንቅስቃሴዎችን በመተቸት የተሰራው «ካሎ ካሚያራ» ይጠቀሳሉ።
የአርቲስቱን መልዕክት ተከትሎ በማህበረሰቡ ውስጥ የተለያዩ አስተያየቶች እየተንጸባረቁ ይገኛሉ።
አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ቡንጌ ለህዝብ መብትና ማንነት በግልጽ በመሟገት የሚታወቅ እንደሆነ ገልጸው በስራውና በአቋሙ ላይ የሚሰነዘሩ አንዳንድ ትችቶችንና የቃላት ፍጥጫዎችን እንደማይቀበሉ ገልጸዋል።
ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች ደግሞ በማህበረሰብ ውስጥ የሚታዩ ማንኛውም ዓይነት መደብ-ተኮር መገለሎችና አለመግባባቶች በሰብአዊ ክብር፣ በመከባበር፣ በመቻቻል እና በእውቀት ላይ በተመሰረተ ግልጽ ውይይት መፈታት እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።
አርቲስት ቡንጌ ቡሩንጄ ችግሩ በከንቲባውና በአስተባባሪ አካላት አማካኝነት መፈታቱን እና ወደ ሥራ መመለሳቸውን በመግለጽ ይቅርታ የጠየቀ ቢሆንም የህብረተሰቡ ውይይት ግን ከግለሰባዊ አለመግባባት አልፎ በማህበረሰብ መስተጋብር ላይ ያተኮረ ሆኗል።
በውይይቱ የተንጸባረቁት የማህበረሰቡ አስተያየቶች እንደሚያሳዩት፤ በማህበረሰብ ውስጥ የሚታዩ የመገለልና የመከፋፈል አዝማሚያዎች ሙሉ በሙሉ እንዲወገዱ፣ ማንም ሰው በመደብ ወይም በሌላ ምክንያት እንዳይገለል እንዲሁም የህጻናትና የዜጎች መብትና ክብር እንዲጠበቅ ጉዳዩ በመከባበር፣ በመቻቻል እና በግልጽ ውይይት በዘላቂነት መፈታት እንዳለበት የህብረተሰቡ ፍላጎትና መልዕክት ነው። በዚህ ጉዳይ የእርስዎ አስተያየት ምንድነው ? ዘላቂ መፍትሔውስ?