1795038055999

የእስራኤል የህክምና ባለሙያዎች ቡድን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በጌዴኦ ዞን ወናጎ ከተማ ለስድስት ተከታታይ ቀናት ባካሄደው የበጎ ፈቃድ የህክምና ተልዕኮ ለ5,448 ታካሚዎች ነጻ የምክርና የህክምና አገልግሎት በመስጠት ተልዕኮውን በስኬት ማጠናቀቁ ተገልጿል።

​ከህዳር 8 እስከ 13 ቀን 2019 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በተካሄደው በዚህ የሰብአዊ ተልዕኮ ላይ ዶክተሮች እና ነርሶች የተሳተፉ ሲሆን፤ የህጻናት፣ የውስጥ ደዌ፣ የማህፀንና ጽንስ፣ የቆዳ፣ የአእምሮ፣ የጥርስ፣ የዓይን እና ሌሎች አስፈላጊ የህክምና አገልግሎቶችን ለአካባቢው ማህበረሰብ አበርክተዋል።

​እ.ኤ.አ ከ2005 ጀምሮ ለ21ኛ ዓመት በቀጠለውና በርካታ ዜጎችን ህይወት በታደገው በዚህ ታላቅ ሰብአዊ ተነሳሽነት ጀርባ፤ በአዲስ አበባ በሚኖሩ ቤተ እስራኤላውያን ጥንዶች በተመሰረተውና በሚመራው “ቤተሳይዳ” የተሰኘ የበጎ አድራጎት ድርጅት የሚገኝ መሆኑ ታውቋል።

​ድርጅቱ ከዓመታዊ የህክምና አገልግሎቱ ባለፈ ባለፉት ስምንት ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ ማህበራዊ አስተዋጽኦዎችን እያበረከተ ይገኛል።

​ሁለት የህጻናት ሆስፒታሎችን ገንብቶ እያስተዳደረ የሚገኝ ሲሆን፣ ግንባታው 90 በመቶ የደረሰ ሶስተኛ ሆስፒታልንም ገንብቶ ለመንግስት አስረክቧል።

​ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ በዓመት ወደ 60 ሚሊዮን ብር በሚገመት በጀት ለአርሶ አደሮች የሚውል የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማካሄድ፣ ከ70 በላይ የንጹህ መጠጥ ውሃ ጉድጓዶችን መቆፈር እና በርካታ የትምህርት ፕሮጀክቶችን በመተግበር ተጨባጭ የልማት ውጤቶችን አስመዝግቧል።

​በእስራኤል የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኤምባሲ ይህንን ትልቅ የበጎ አድራጎት ሥራ ለሩት የ“ቤተሳይዳ” ድርጅት መስራቾች፣ ጊዜያቸውንና እውቀታቸውን በመስዋዕትነት ለሰጡ የእስራኤል ሐኪሞች ቡድን አባላት እንዲሁም የትውልድ ሀገራቸውን ህዝብ ለመደገፍ ሁሌም ግንባር ቀደም ለሆኑ ቤተ እስራኤላውያን በሙሉ ልባዊ ምስጋናውን አቅርቧል።

​WT Media (የተገለሉ ማህበረሰቦች ድምፅ) ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሰብአዊ ስራዎችን እና የጤና ድጋፎችን በቀጣይነት በመከታተል ለአንባብያን የሚያደርስ ይሆናል።