በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ሀብሩ ወረዳ በሚገኘው የጃራ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ በመምህራን እጥረትና በበጀት እጦት ምክንያት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸውን በመጠለያ ጣቢያው የሚገኙ ተፈናቃዮች ገልጸዋል።
ከሁለት ሺህ ስምንት መቶ በላይ ተማሪዎች ካሉት መጠለያ ጣቢያ ከአንድ ሺህ አምስት መቶ በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች ዘንድሮ ወደ ትምህርት ቤት አልሄዱም። የመጠለያ ጣቢያው ነዋሪዎች «አንደኛ ክፍል፣ አምስተኛ ክፍል እና ስድስተኛ ክፍል» ትምህርት ቤት ሄደው እንደማያውቁ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል።
በመጠለያ ጣቢያው ውስጥ ያለው ትምህርት ቤት በመዘጋቱ የተነሳ ከሰባት ኪሎ ሜትር በላይ በእግር ተጉዘው የሚማሩ ተፈናቃዮች ለፆታዊ ጥቃት እና ለሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ሰለባ መኾናቸው ይነገራል።
የሀብሩ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት በአሁኑ ወቅት ለመጠለያ ጣቢያው የተያዘ በጀት እንደሌለ ገልጧል።
ከዚያ በተጨማሪ በመጠለያ ጣቢያው የረድኤት ተቋማት ድጋፍ ባለመኖሩ ትምህርት ማስቀጠል ፈታኝ መኾኑን አሳውቋል።
በጃራ መጠለያ ጣቢያ ባለፉት ስድስት ዓመታት ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ተፈናቅለው በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ከ30 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ይገኛሉ።