አዲስ የተመሰረተው መንግሥት ዘላቂነት ያለውን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አሰራር በመከተል የማይቀለበስ ዕድገት ማረጋገጥ እንደሚጠበቅበት የዎላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዎች አስተያየት ሰጥተዋል ።

ነዋሪዎች አክለውም የማትደፈር ጠንካራ ሀገር ለመገንባት የሚያስችል አንድነት በህዝቦች መካከል እንዲጠናከር ሁሉም በኃላፊነት መንፈስ መሥራት እንዳለበት በአስተያየታቸው ገልፀዋል ።

በከተማው ተዘዋውረን ካነጋገርናቸው መካከል አንዳንዶች ሀገራችን ኢትዮጵያ የብዝሃነት አብሪ ውበትና የተጋመደ ጥንካሬ ውጤት መሆኗን ተናግረው ጥንካሬዋና አንድነቷ ጠላቶቿን ስለሚያስፈራ በሀገር ውስጥ ያሉትን የተዛነፈ የጠጥቂቶችን አመለካከት በመኮትኮት ሀገራችንን ለማዳከም እንደሚንቀሳቀሱ መታወቅ አለበትም ብለዋል ።

ከሠላምና ፀጥታ አንፃርም የፖሊስና ሚሊሺያ ተቋማትን በዲሲፕሊን በማነጽ እና የሠላም አስፈላጊነትን ዜጎች እንዲረዱ በማስተማር የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ቢሠራ መልካም እንደሆነም አስተያየታቸውን አንስተዋል ።

አስተያየት ሰጪዎቹ አያይዘውም መንግሥት ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ተመሳሳይ ተግባራዊነት ያላቸውን አሠራሮች በመዘርጋት የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እንዳይነሱ መትጋት ይጠበቅበታል ብለው ከኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት አንፃር በትምህርትም ሆነ በልምድ ሙያ ያካበቱ ዜጎችን በማቀናጀት ዘላቂ ገቢ እንዲያገኙ መስራት አለበትም ይላሉ ።

በተለያዩ ሥራ ዘርፎች እምቅ ችሎታ ያላቸው ወጣቶች ስራ ዕድል ተጠቃሚ ሚሆኑበት ምቹ ሁኔታ በመፍጠር በትኩረት ቢሠራ እንደ አንድ ዜጋ ለኢትዮጵያ ብልጽግና የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ በመናገር ሀሳባቸውን አክለዋል ።

ለሀገር ህልውና ነፍሳቸውን ያለስስት ለሚገብሩ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ትልቅ ክብር እንዳላቸው በመግለፅ ለሀገር አንድነትና ክብር ህዝብና መንግስት በአንድ ሀሳብ በመንቀሳቀስ የከፍታ ጉዞዋን ሊያፋጥኑ እንደሚገባ ተናገሩ።

በአስተያየታቸው እንደ ኢትዮጵያዊን የመጣውን ለውጥ እንደሚደግፉ ገልፀው አዲስ የተመሠረተው መንግሥት ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ድረስ ተመሳሳይና ወጥ አሰራሮችን በመዘርጋት ለዜጎች የተቀላጠፈ አገልግሎት በመስጠት በሀገራቸው ጥቅም የማይደራደሩ ሀገር ወዳድ ዜጎችን መፍጠር ይጠበቅበታል አሉ ።