መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከመከላከያ ሠራዊት ጐን እንዲቆሙ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ጥሪ አቀረበ
መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከመከላከያ ሠራዊት ጐን በመሆን ለአገራችን ዘብ እንድንቆም ጥሪያችንን እናስተላልፋለን ሲል የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ጥሪ አቀረበ።
የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ዛሬ ባወጣው መግለጫ የአገራችንን ሉዓላዊነት ከማስከበር አልፎ ሕዝባችን ድጋፍ በፈለገበት መስክ ሁሉ በመሰማራት የቁርጥ ቀን ልጅ የሆነውን የመከላከያ ሰራዊታችንን መተናኮስ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊታገሰው የማይችለው እኩይ ተግባር ነው ብሏል።
ምክር ቤቱ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን ጎን በመቆም የአገራችንን ሉዓላዊነት እና አንድነት የምናስጠብቅበት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን ሲል በማኅበራዊ ገጹ አስታውቋል።
