ሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳይ በማስመልከት ከወላይታ ዞን አስተዳደር የተሰጠ መግለጫ

ህወሃት በትግራይ ክልል በሚገኘው የሀገራችን መከላከያ ሰራዊት ላይ ያደረሰውን ጥቃት በጽኑ እንደሚያወግዝ የዞኑ አስተዳደር ይገልጻል፡፡


በማያያዝም ህወሃት ያሰማራው የታጠቀ ኃይል ያደረሰውን ጥቃት መነሻ በማድረግ የሀገራችን መከላከያ ኃይል እርምጃ እንዲወስድ የኢፌዴሪ ጠ/ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ባስተላለፉት ትዕዛዝ መሰረት የሀገራችን መከላከያ ኃይል እየወሰደ ያለው እርምጃ የሀገራችንን ሉዓላዊነትና ክብርን ለማስጠበቅ የሚወሰድ ተገቢና ትክክለኛ እርምጃ እንደሆነ የዞኑ አስተዳደር ያምናል ፡፡
ስለሆነም የሀገራችን ኩራት በሆነው መከላከያ ኃይል ላይ የደረሰው ጥቃት የሀገራችንን ክብርና ስም ዝቅ ለማድረግ ታስቦ የተደረገ በመሆኑ መላው ህዝባችን ከመከላከያ ጎን በመቆም ይህን እኩይ ተግባር ለመፈጸም የተነሳውን ኃይል አደብ ሊያስገዛ እንደሚገባም ተጠቁሟል፡፡
እንዲህ አይነት እኩይ ተግባር ለመፈጸም የሚቃጣ ኃይል በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የራሱን መረብ ዘርግቶ የሚንቀሳቀስ የጥፋት ኃይል ስላለ የዞናችን ህዝብ እና አጠቃላይ የፀጥታ መዋቅር አካባቢውን ተግቶ እንዲጠብቅ ጥሪ አቅርቧል፡፡