========

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሳይንስና ከፍተኛ ት/ት ሚኒስቴር ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በሰላምና የልማት ተግባራት ላይ በማተኮር በተለይም ማንኛውም ግጭት አስቀድሞ እንዳይፈጠር ብሎም የሰላም መታወክ ሲፈጠርም ቀውሱን ተቋቁመው ተልዕኳቸውን ማስካት እንዲችሉ በአደረጃጀት ደረጃ “የሰላምና የልማት አማካሪ ምክር ቤት” እንዲያቋቁሙ አቅጣጫ ማስቀመጡ ይታወሳል።

በዛሬው ዕለት በተካሄደው የምክክር መድረክ የተገኙት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕ/ር ታከለ ታደሰ እንደገለጹት፤ ተቋማችን ከዚህ ቀደም ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመምከር ለሰላማዊ መማር ማስተማር በስፋት ሲሰራ ቆይቷል፣ የተሻለ ውጤትም ተመዝግቧል ብለዋል።

የሳይንስና ከፍተኛ ት/ት ሚኒስትር መስሪያ ቤት ያስቀመጠውን አቅጣጫ በመከተልም 14 አባላት ያሉት “የሰላምና ልማት አማካሪ ምክር ቤት” መቋቋሙን ገልጸው፤ እንደ ተቋም የሚገጥሙ ችግሮችን በብቃት ለመፍታትም የአካባቢውን ማህበረሰብና አስተዳደር አካላት፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ እንዲሁም የጥበቃና ደህንነት መዋቅር የተካተቱበት አባላት በተቋቋመው ምክር ቤት መሳተፋቸውን ፕ/ር ታከለ አሳውቀዋል።

የተረጋጋና ሰላም የሰፈነበት መማር ማስተማርን ለማዝለቅ የምክር ቤቱ አባላት ሚና ጉልህ መሆኑን የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ፤ የተቀናጀና ንቁ ተሳትፎ በማድረግ በየወቅቱ የስጋት ምንጮችን በመለየት ችግሮች ሲፈጠሩም የጋራ ርብርብ በማድረግ አስቀድሞ የመከላከል ስራን ለመስራት ምክር ቤቱ ሚናው ጉልህ እንደሆነም ፕ/ር ታከለ አውስተውል።

ዩኒቨርሲቲያችን ከአካባቢው ማህበረሰብና ባለድርሻ አካላት ጋር የጀመረውን የሁለትዬሽ ግንኙነት ከማጠናከርም ባለፈ፤ ከተቋቋመው አማካሪ ምክር ቤት ጋር የጋራ ዕቅድ አውጥቶ ዘላቂ ሰላምን በማስፈን የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ይሰራል ሲሉም ፕሬዝዳንቱ አሳውቀዋል።

አማካሪ ምክር ቤቱ ከአካባቢው ማህበረሰብ በቅርበት ተሳስረው በመስራት የተቋሙን ተልዕኮና ግብ ከማስፈጸም ባሻገር በልማት መስኮች የህዝብ ተጠቃሚነት እውን እንዲሆን አዎንታዊ ድርሻ ይኖረዋል ሲሉ በምክክር መድረኩ የተገኙት የዩኒቨርስቲው አስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር አብርሃም ቦሻ ተናግረዋል።

ዶ/ር አብርሃም አክለውም ዩኒቨርሲቲያችን የተሰጠውን ተልዕኮ በብቃት እንዲወጣ በማድረግ ብሎም የአካባቢውን ማህበረሰብ በንቃት በማሳተፍ የተረጋጋና ሰላማዊ አካባቢን በመፍጠር በመማር ማስተማር፣ በችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር፣ በማህበረሰብ አገልግሎት እና በቴክኖሎጂ ሽግግር ስርጸት መስክ ውጤታማ ስራ ለመስራት ምክር ቤቱ ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

ለምክር ቤቱ አባላት የውይይት መነሻ ሀሳብ ይሆን ዘንድ በዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕ/ር ታከለ ታደሰ ሰነድ የቀረበ ሲሆን፤ የምክር ቤቱ በዚህ መልኩ መደራጀትና ወደ ስራ መግባት በተቋሙ ውስጥና በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት ሰፍኖ የተቋሙን ተልዕኮ በተገቢው ለማሳካት ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ይኖረዋልም ተብሏል።

ምክር ቤቱ የራሱን መሪ እቅድ አዘጋጅቶ መደበኛ ተግባራትን በመከታተልና በመደገፍ ከሚወጣው ኃላፊነት ባሻገር፤ በተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎችን በማስተባበርና በማመቻቸት ለህብረተሰቡ ዘላቂ ተጠቃሚነት እንደሚሰራም በአውደ ምክክሩ ተጠቁሟል።

በበጎ አድራጎት ስራው “አንድ ቅዳሜ ለማህበረሰቤ” ፣ “የዩኒቨርሲቲው ልጄ” ፣ “የቃል ኪዳን ቤተሰብ ምስረታ”፣ ” የማህበረሰብ ቀን” የተሰኙ ርዕሰ ጉዳዬች መካተታቸውም ታውቋል።

በዛሬው እለት ከዩኒቨርሲቲው “የሰላምና ልማት አማካሪ ምክር ቤት” አባላት ጋር በተካሄደው ምክክር በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዬች ላይ ሰፊ ውይይት የተካሄደ ሲሆን፥ ከአባላቱ ለተነሱ ጥያቄዎችም ምላሽ ተሰጥቷል።

ምክር ቤቱ በየወሩ የራሱን መደበኛ ስብሰባ የሚያላሄድ ሲሆን፤ የዩኒቨርሲቲው ስራ አመራር ቦርድም የአማካሪ ምክር ቤቱን የእቅድ አፈጻጸም በየሶስት ወሩ እየተከታተለ እንደሚገመግም በምክክር መድረኩ ተገልጿል ሲል የዩንቨርስቲው ኮሙኒኬሽን ዳይሮክተሬት ዘግቧል።