

በክልላችን የጸጥታ ሁኔታን አስመልክቶ የተሰጠ ተጨማሪ ማብራሪያ
መንግስት በመላ ሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየሰራ ይገኛል።
ሀገራችን በውስጥም ሆነ በውጭ ያጋጠማትን ፈተናና ጫና ተቋቁማ የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተጀመረው ጥረት በህዝቦቻችን የላቀ አንድነት እና ትግል ወደምንፈልገው የእድገት ጉዞ ከፍ ማለታችን አይቀርም።
በእርግጥ ድህነትን ታሪክ ለማድረግ በሚካሔደው እንቅስቃሴ የሚያጋጥመው ፈተና በርካታ ነው። በሌላ በኩል የውጭም ሆነ የሀገር ውስጥ ጠላቶቻችን ሀገሪቱ እንዳትበለጽግ እና ዜጎች የተረጋጋ ኑሮ እንዳይመሰርቱ ለማድረግ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም።
የተጀመረው ለውጥ ያላስደሰታቸው የግል እና የቡድን የፓለቲካ ትርፍ ለማግኘት ያለሙ ሀይሎች ዜጎች በየ እለቱ የስጋት ቀጠና ላይ እንዲወድቁ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
ከክልላችን የጸጥታ ሁኔታ ጋር በተያያዘ የክልሉን መንግስት አቋም እና የጸጥታ ችግር በተስተዋለባቸው አካባቢዎች ሰላም ለማስፈን እየተደረገ ያለውን ጥረት አስመልክቶ ሰሞኑን ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ መስጠታችን ይታወሳል።
በዚሁ መሠረት በክልሉ በኮንሶ ዞን ፣በአሌ፣በደራሼ እና በአማሮ ልዩ ወረዳዎች የጸጥታ ችግሮች መኖራቸውን ለህዝብ ይፋ እንዲሆን አድርገናል።
በኮንሶ ዞን እና በአሌ ልዩ ወረዳ የወሰን ጉዳይን አስመልክቶ የተከሰተ የጸጥታ ችግር ሲሆን።
ቀደም ሲል የግጭት መንስኤ የሆነውን የወሰን ማካለል ጉዳይ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት እየተሰራ ባለበት ሂደት ላይ እያለ የተከሰተ የጸጥታ ችግር ነው።
በደራሼ ልዩ ወረዳ ደግሞ የተከሰተው የጸጥታ ችግር ከመዋቅር ጥያቄ ጋር የተያያዘ መሆኑንም መግለጻችን ይታወሳል።
የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የክልሉ መንግስት ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል።
መንግስት ህብረተሰቡን በማሳተፍ ችግሮችን በውይይት እና በሰከነ መንገድ ለመፍታት የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።
ዛሬ እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ክልል የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች ማለፍ የምንችለው የጋራ አንድነታችንን በማጠናከር ይሆናል።
የሀገራችን የለውጥ ጉዞ ያላስደሰታቸው እና የግል ጥቅማቸውን ለማስከበር የሚጥሩ ሀይሎች የህዝብን ጥያቄዎች ተገን በማድረግ ዘወትር የብጥብጥ አጀንዳ እየቀረጹ ህብረተሰቡ ተረጋግቶ እንዳይኖር በማድረግ ላይ ናቸው።
ህዝቡ ችግር ናቸው ብሎ ያቀረባቸውን ጥያቄዎች በመነጋገር ፣በመወያየት እንዲሁም ህግና ስርዓትን ተከትሎ ለመፍታት የክልሉ መንግስት አቅዶ እየሰራ ይገኛል።
በሌላ በኩል በአማሮ ልዩ ወረዳ እና በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ጉጂ ዞን አዋሳኝ አካባቢዎች መሽጎ የነበረው የጠላት ሀይል በሰዎች እና በንብረት ላይ ከፍተኛ ኪሳራ እያደረሰ ይገኛል።
ችግሩን ለመፍታትም የክልሉ መንግስት የጸጥታ አካላትን ወደ ስፍራው በመላክ ከህዝቡ ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ ሲሆን ከኦሮሚያ ክልል እና ከፌደራል መንግስት ጋር በመነጋገር ህብረተሰቡ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው ።
በአካባቢው የመሸገው ይህ የጠላት ሀይል የሰው ህይወት እንዲያልፍ፣ የአካል ጉዳት እንዲሁም የንብረት ውድመት እንዲደርስ ምክንያት ሆኗል።
የክልሉ መንግስትም በህብረተሰቡ ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍ ለመታደግ በልዩ ትኩረት እየሰራ ይገኛል።
በሌላ በኩል ትላንት ሚያዝያ 1 ቀን 2014 ዓም /ኢፕድ/ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የደቡብ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሰናይት ሰለሞንን ጠቅሶ በፌስቡክ ገጹ እና በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ በኮንሶ ዞን፣በአሌ፣በደራሼ እና በአማሮ ልዩ ወረዳዎች ላይ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር አስመልክቶ ባወጣው ዘገባ ላይ ጸሀፊው መሰረታዊ የመረጃ ስህተት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል።
በዘገባው በክልሉ የሚገኙ የዞን እና የልዩ ወረዳዎችን መዋቅሮች በትክክል ከመግለጽ ጀምሮ በዜናው ይዘት ላይም የሀሳብ መፋለስ አጋጥሟል። የተፈጠረውን ስህተት ከኢፕድ ጋር በመነጋገር ዜናው እንዲታረም ጥረት ተደርጓል።
ዜናውን አስመልክቶ በርካታ የፌስቡክ ተከታታዮቻችን በውስጥ መስመር ተጨማሪ ማብራሪያ እንድንሰጥ በጠየቁን መሰረት ይህንን መረጃ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
ስለሆነም በተቋማችን በኩል የተፈጠረ የመረጃ ስህተት አለመኖሩን መላው የክልላችን ነዋሪዎች እንዲገነዘቡ ለማሳወቅ እንወዳለን።
በክልላችን በኮንሶ ዞን፣በአሌ፣በደራሼ እና በአማሮ ልዩ ወረዳዎች ላይ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር አስመልክቶ ያለውን ነባራዊ ሁኔታና የክልሉ መንግስት ሰላም ለማስፈን እያደረገ ያለውን ጥረት አስመልክቶ በቀጣይ ለህዝባችን ተከታታይ መረጃ የምንሰጥ ይሆናል።