

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከፍተኛ አመራሮች ከጎንደር ከተማ የእምነት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ጋር ዛሬ የጋራ ምክክርና ውይይት አካሂደዋል፡፡
የኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ኡመር እድሪስ በመድረኩ እንዳሉት የእስልምና እና የክርስትና ሃይማኖቶች ለብዙ ሺህ አመታት አብረው በጋራ የኖሩና የእምነቶቹ ተከታዮችም የጋራ የአብሮነት እሴቶች የገነቡ ታላላቅ ሃይማኖቶች ናቸው፡፡

የሰው ልጅ የሃይማኖት እምነት አለም ከተፈጠረ ጀምሮ ያለ እና የነበረ ወደፊትም የሚኖር መሆኑን ጠቅሰው፤ ሰላም ለሰው ልጆች የህልውና መሰረት በመሆኑ ሁሉም ሃይማኖቶች ለሰላም በአንድነት እንዲቆሙ አሳስበዋል፡፡
”በጎንደር በተፈጠረው ችግር አዝኛለሁ ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ነገር ግን ከመጣሁ በኋላ በውይይት መድረኩ የሁለቱ ሃይማኖቶች ተከታዮች ያሳዩት የአብሮነት፣ የመከባባርና ወንድማማችነት ስሜት ከልብ አስደስቶኛል” ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር በመቀናጀት በግጭቱ የተጎዱ ወገኖችን በመደገፍና የፈረሱ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
”በጎንደር ከተማ በሃይማኖት ሽፋን የተፈጠረው ችግር ከተማዋን ታሪካዊነት የማይመጥንና በሰዎች ህይወትና ንብረት ላይም የደረሰው ጉዳትና ጥፋት አሳዛኝ ነው” ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብጹዕ አቡነ ዮሴፍ ናቸው፡፡

”ሀገርን እንደ ሀገር ለማስቀጠል አስተሳሰባችንን በበጎነት መቃኘት አለብን” ያሉት አቡነ ዮሴፍ፤ የሰላም ባለቤት ፈጣሪ ቢሆንም እኛ የሰው ልጆች በምናደርገው በጎ ነገር ሰላምን ማረጋገጥ እንችላለን ሲሉ ገልፀዋል።
”ለልጆቻችን በጎና አስተማሪ የሆነ መልካም ነገር ትተን ማለፍ የምንችለው እኛ ወደ ልባችንና ወደ ቀልባችን ስንመለስ ነው” ያሉት ዋና ፀሐፊው፤ በሃይማኖት ስም የሚነግዱትን በጋራ ተዉ ብለን መገሰጽና መምከር አለብን ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት ፕሬዚዳንት ፓስተር ጻዲቁ አብዶ በበኩላቸው ሁላችንም ከሰላም እንጂ ከግጭት ተጠቃሚ መሆን እንደማንችል መገንዘብ አለብን ብለዋል፡፡
ብሔርም ሆነ ሀይማኖት ዛሬ አልተፈጠሩም ያሉት ፓስተር ጻዲቁ፤ ሀገራችንን የሰላም፣ የፍቅርና የመከባበር ምሳሌ በማድረግ አንዱ የሌላውን የእምነት ተቋም በመገንባት አብሮነትን በተግባር ልናሳይ ይገባል ሲሉ መግለፃቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።
ተሳታፊዎቹ በውይይቱ ማጠቃለያ የሁለቱን እምነቶች አብሮነት የሚያጠናክሩና ችግሩን በዘላቂነትና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚያስችል ባለ 5 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት አጠናቀዋል ስል ኢፕድ ዘግቧል።