ዩኒቨርሲቲው በዓለም አቀፍ ግንኙነት መስክ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በትብብር የሚሰራቸውን የሁለትዮሽ የትምህርትና የልማት ተግባራት አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል የዩንቨርስቲው ፕረዚዳንት ፕ/ር ታከለ አሳውቀዋል።

የዩኒቨርሲቲው 2014 ዓ.ም በተቋም ደረጃ የጥናትና ምርምር እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሽግግር ስራዎችን ለማሳካት ከያዛቸው ግቦች አንደኛው ከውጭና የአገር ውስጥ ተቋማት እና ኢንዱስትሪዎች ጋር በጋራ ምርምሮችን እና ፕሮጀችክቶችን ለማካሄድ እቅድ ተይዞ ወደ ስራ እንደተገባ ነው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕ/ር ታከለ ታደሰ የገለጹት።

በ2014 ዓ.ም ከውጭና የአገር ውስጥ ተቋማት እና ኢንዱስትሪዎች ጋር በጋራ 30 የምርምር ስራዎችን ለማከናወን እቅድ መያዙን የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ፤ 20 የተለያዩ የምርምር ስራዎች ከተቋማቱ ጋር ተግባራዊ መደረጉን ጠቁመዋል።

ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር 2 ስልጠናዎች በጋራ ለማዘጋጀት ታቅዶ ሙሉ በሙሉ መሳካቱን የገለጹት ፕ/ር ታከለ፤ በምርምር መስክ ከተቋማቱ ጋር የተፈጠሩ ትስስሮች በቁጥር ወደ 6 ከፍ ማለቱንም አብራርተዋል።

በበጀት ዓመቱ በ 9 ወራት አራት ያህል የቴክኖሎጅ ሽግግር ስራዎች በትስስር የተተገበሩ መሆናቸውን ፕሬዝዳንቱ ገልጸው፤ 15 ያህል ችግር-ፈቺ የምርምሮች ከአጋር ድርጅቶች ጋር በተደረገ በትስስር መተግበሩም ተገልጿል።

ዩኒቨርሲቲው ለሳይንስና ማህበረሰብ አገልግሎት እንዲውል ከአጋር ድርጅቶች ባለፉት ዘጠኝ ወራት 35 ሚሊየን ብር ለማሰባሰብ እቅድ መያዙን ገልጸው፤ በአጠቃላይ 31 ሚሊየን ብር ሀብት መገኘቱን ፕሬዝዳንቱ አሳውቀዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከአለም አቀፍ ተቋማት ጋር 40 ያህል የመግባቢያ ሰነድ የተፈራረሙት መሆኑን ፕሬዝዳንቱ አሳውቀው፤ ከነዚህም ውስጥ 16ቱ ወደ ስራ መግባታቸውና ቀሪ 24ቱ ደግሞ በሂደት ላይ መሆናቸውን ፕ/ር ታከለ አሳውቀዋል።

ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ከ16 ዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በንቃት እየሰራ መሆኑን የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ፤ ተቋማቱ በቴክኖሎጂ ሽግግር፥ በአካዳሚክ ሰራተኞች ልውውጥ፥ በተማሪዎች ልውውጥ፥ በዶክትሬት እና ማስተር ፕሮግራሞች ስኮላርሺፕ፥ በልምድ መጋራት፥ በጋራ ትምህርታዊ እና የምርምር ስራዎች፥ በአለም አቀፍ ፕሮጀክቶች፥ በሲምፖዚየም፣ ኮንፈረንስ እና ሌሎች ሳይንሳዊ እንቅስቃሴዎችን በማዘጋጀት፣ የጋራ የአካዳሚክ ዲግሪ፣ በማስተር እና በዶክትሬት ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት፥ የአጭር ጊዜ የትምህርት መርሃ ግብሮች በጋራ የማዘጋጀትና መሰል መርሃ ግብሮችን በማዘጋጀት ትኩረት ሰጥተው ይሳታፋሉ ሲሉ ጠቅሰዋል።

ከዩኒቨርሲቲው ጋር በአጋርናት ለመስራት ተፈራርመው ወደ ሥራ ያልተገቡ 24 አለም አቀፍ ተቋማት ጋር በአካዳሚክ ሰራተኞች ልውውጥ፥ በተማሪ ልውውጥ፥ በዶክትሬት እና ማስተርስ የትምህርት ፕሮግራሞች ስኮላርሺፕ፥ በልምድ መጋራት፥ በጋራ የምርምር ፕሮጀክቶች ግምገማ እና መሰል ተግባራት ላይ በትብብር ለመስራት የዝግጅት ምዕራፍ ላይ መሆናቸውንም ፕሬዝዳንቱ አሳውቀዋል።

በሀገረ ስፔን የሚገኘው ቫሌንሲያ ዩኒቨርሲቲ፥ የፖላንዱ ክራኮው ግብርና ኮሌጅ፥ የአለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት፥ ጣሊያን የሚገኘው ሳን ጋሊካኖ ኢስቲትዩት IRCCS(IFO-ISG)፣ አሜሪካ የሚገኘው ስም ፓወር፣ ጣሊያን የሚገኘው የበርጋሞ ዩኒቨርሲቲ፣ ቼክ ሪፑብሊክ ማሳራይክ ዩኒቨርሲቲ፥ ቤልጂየም የሚገኘው አንትወርፕ ዩኒቨርሲቲ፥ ስፔን የሚገኘው ጁንታ ዴ ካስቲላ እና ሊዮን፥ የፈረንሳይ ኤምባሲ፥ ስፔን የሚገኘው የማድሪድ ኦቶኖማ ዩኒቨርሲቲ፥ አየርላንድ የሚገኘው የዱብሊን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ (ዩሲዲ)፥ የሕንድ ቻንዲግራህ ዩኒቨርሲቲ፥ የፖላንድ ኦፖሌ ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ እና በሩሲያ የሚገኘው አስትሮኖሚካል ሳይንሳዊ ማዕከል የጋራ አክሲዮን ኩባንያ ከዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ጋር በአጋርነት እየሰሩ ያሉ 16 ዓለም አቀፍ ተቋምት መሆኑን የዩኒቨርስቲው ኮሙኒኬሽን ዳይሮክተሬት የላከልን መረጃ ያመለክታል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *