

(በአቶ ዋና ዋጌሾ)
“በዎላይታ አውራጃ በኮይሻ ወረዳ በዋጪጋ መንደር ከዎላይታ ቤተሰብ የተወለዱ አቡነ ጴጥሮስ በአስከፊው ጦርነት ውስጥ ለምርኮ የበቁት ገና በልጅነት ዕድሜአቸው ነበረ፡፡ አቡነ ጴጥሮስ ከክርስትና ስማቸው በፍት በልጅነታቸው #አላንቦ ተብለዉ ይጠሩ ነበረ።
ልዑል ራስ ካሳ አቡኑን እንደ ምርኮኛ ሳይሆን እንደ ልጃቸው በመመልከት በእንክብካቤ እያስተማሩ አሳድገው የግምጃ ቤታቸው ሃላፊና ፀሐፊ አድርገው ሾምዋቸው፡፡ በሥራ ቅልጥፍናቸውና ፍፁም ታማኝነታቸው የረኩት ልዑል ራስ ካሳ ከአጠገባቸው እንዳይርቁ በጋብቻ ሊያስሩዋቸው ሲሞክሩ አቡኑ ፍላጎታቸው አለማዊ ሕይወት እንዳልሆነና ምኞታቸው ምንኩስና መሆኑን ይገልጹላቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት አፄ ምኒልክ በብሔርና በጎሣ ተለያይታ የነበረችውን ኢትዮጵያ አንድ የማትበገር ሃያል አገር ለማድረግ ካላቸው ጽኑ ፍላጎት በመነሳት እሺ ያለውን በስብከት እንቢ ያለውን በጦር ሃይል በማስገደድ አንድነትን ለመፍጠር በሚታትሩበት ወቅት በዎላይታ በኩል ያደረጉዋቸው ተደጋጋሚ ድፕሎማሲያዊ ጥረቶች ባለመሳካታቸው ወደ ሃይሉ አማራጭ ማዘንበላቸውን ከታሪክ እንረዳለን፡፡
በዚሁ የሃይል እርምጃቸው ጦርና የጦር መሪዎችን እያፈራረቁ አምስት ጊዜ ያካሄዱት የወረራ ሙከራዎች ባለመሳካታቸውና በስድስተኛው ጊዜ ከብዙ ሠራዊት ጋር የተላኩት የጦር ሚኒስትሩ ራስ መንገሻ አትክም ጭራሽ ለከፋ ሽንፈት በመዳረጋቻዉ አፄ ምኒልክ ተበሳጭተው በ1887 ዓ.ም ወደ ዎላይታ ለመዝመት ክተት አውጀው ነጋሪት አስጎስመው ወደ ዎላይታ አመሩ፡፡
በወጣው የውጊያ ዕቅድ መሠረት ከተለያዩ ማዕዘናት (ዙሪያ ከበባ) ጦራቸውን አሰልፈው የንጉሡን ትዕዛዝ በተጠንቀቅ የሚጠባበቁት የራስ ወልደጊዮርጊስ፣ የደጃዝማች ገነሜ፣ የራስ ልዑልሰገድ፣ የደጃዝማች በሻህና የልዑል ራስ ካሳ ጦሮች በአንደኛው ግንባር ደግሞ ንጉሡ እራሳቸው ከሚመሩት ጦር ጋር በአንዴና በሕብረት ባካሄዱት ጦርነት ከሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች (ከአፄ ምኒልክና ከንጉሥ ጦና) ብዙ ሕይወትና ንብረት ጠፍቶ በአፄ ምኒልክ አሸናፊነት ጦርነቱ ተደመደመ፡፡


ከውጊያው በኋላ የሆነው ሁሉ ዘግናኝና ከንጉሡ ቁጥጥር ውጭ መሆኑን ታሪክ ያስረዳል (በጻፍኩት ‹የዎላይታ ሕዝብ ታሪክ› መጽሐፍ የውጊያው ዝርዝር ሁኔታ ተመልክቷል) የዚህ ጽሑፍ ዓላማ የዎላይታን ጀግንነት ወይም በዘመናዊ መሳሪያና ትጥቅ የተዋጋውን የንጉሡን ሠራዊት የውጊያ ጥበብ ለመዘከር ሳይሆን ውጊያውን ተክትሎ ወታደሩ በሕዝቡ ላይ መጠነ ሰፊ የበቀል ርምጃ እየወሰደ በነበረበት ወቅት እንደ ዕድል በራስ ካሳ እጅ ለወደቁት የአቡነ ጴጥሮስ አመጣጥ ከአባቶች ከሰማሁት ባሻገር እኔም በአካል ብፁእነታቸውን አግኝቼ ከአጫወቱኝ በመነሳት እየተንጋደደ ውሉን በመሳት ላይ ያለውን የብፁዕነታቸውን ማንነት ለወገኖቼ ለማሳወቅ ነው፡፡

በዎላይታ አውራጃ በኮይሻ ወረዳ በዋጪጋ መንደር ከዎላይታ ቤተሰብ የተወለዱ አቡነ ጴጥሮስ በአስከፊው ጦርነት ውስጥ ለምርኮ የበቁት ገና በልጅነት ዕድሜአቸው ነበረ፡፡ ልዑል ራስ ካሳ አቡኑን እንደ ምርኮኛ ሳይሆን እንደ ልጃቸው በመመልከት በእንክብካቤ እያስተማሩ አሳድገው የግምጃ ቤታቸው ሃላፊና ፀሐፊ አድርገው ሾምዋቸው፡፡ በሥራ ቅልጥፍናቸውና ፍፁም ታማኝነታቸው የረኩት ልዑል ራስ ካሳ ከአጠገባቸው እንዳይርቁ በጋብቻ ሊያስሩዋቸው ሲሞክሩ አቡኑ ፍላጎታቸው አለማዊ ሕይወት እንዳልሆነና ምኞታቸው ምንኩስና መሆኑን ይገልጹላቸዋል፡፡
ይህ በጊዜው በራስ ካሳ ተቀባይነት ባለማግኘቱ አቡኑ ደጃዝማች ተፈሪ መኮንን እንዲያማልዱዋቸው ይማጸናሉ፡፡ በወቅቱ የባሶ ገዢ የነበሩት ደጃዝማች ተፈሪ መኮንን (በኋላ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ተብለው የኢትዮጵያ ንጉሥ) ልዑል ራስ ካሳን አስፈቅደውላቸው አቡኑ ለመመንኮስ በቁ፡፡
አቡኑ ከምንኩስናቸው በኋላ በደብረሊባኖስ ገዳም ከካህናቶች ጋር በትህትና ሲያገለግሉ ቆይተው የቤተክህነት ሹመት አግኝተው በትውልድ አገራቸው በዎላይታ የአቡነ ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን ሊቀመምህር ሆነው ለአመታት አገልግለዋል፡፡
ከዚያም በዝዋይ ደሴቶች አገልግለው ወደ ደብረሊባኖስ በመመለስ በእጬጌነት ሲያገለግሉ ሳሉ ታሪካቸውን ከመሠረቱ በሚያውቁ በግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ድጋፍ ሊቀ ጳጳስ ሆነው በተመረጡበት የሹመት መንበር ሊቀመጡ ችለዋል፡፡
የአቡነ ጴጥሮስን ታሪካዊ አመጣጥ ከታሪክ ያጠናው ማርሻል ግራዘያኒ ለመሰሪ ዓላማው ሊጠቀምባቸው አስቦ በዎላይታነታቸው በደል እንደደረሰባቸውና በማስደሰት ለኢጣሊያ መንግሥት ከሠሩ ከፍ ከፍ አድርጎ እንደሚሾማቸው ይነግራቸዋል፡፡ ሕዝቡ የጣሊያንን ገዥነት እንዲቀበል እንዲሰብኩላቸውም ይጠይቋቸዋል፡፡
አቡኑ በግላቸው ምንም በደል እንዳልደረሰባቸው ይልቁንም በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ በደል እየፈጸመ ያለው የኢጣሊያ መንግሥት በመሆኑ እንኳን ሕዝቡ መሬቷም እንዳትሸከማቸው ያወገዙ መሆናቸውን ይነግሯቸዋል፡፡
በዚሁ ውግዘታቸው ናላው የዞረው ግራዚያኒ እንዲረሸኑ ይወስናል፡፡ ብፁዕነታቸውም ለሀገራቸው መስዋዕት በመሆን በጠላት መትረየስ ያለ ርህራሄ ተረሸኑ፡፡ በታሪክ አጋጣሚ በአካባቢው ስለነበርኩ ይህንን መጥፎ ድርጊት በአይኔ ተመልክቻለሁ፡፡
ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በግፍ ከተረሸኑ በኋላ በዱር በገደል የተሰማራው የኢትዮጲያ ጀግና አርበኛ ሁሉ ኃይላቸውን አጠናክረው ኢጣሊያኖችን መግቢያ መውጫ ከልክለው ሲያርበተብቱዋቸው ሳለ በእንግሊዝ የሚመራ የቃል ኪዳን ወታደሮች ቡድን ደርሶ በሕብረት ጣሊያኖችን ወግተው ሀገሪቷ ሙሉ ነፃነትዋን ከተጎናጸፈች በኋላ ለሀገራቸው መስዋዕት የሆኑ የክፉ ቀን ጀግች ልጆችዋን በማስታወስ ለምሳሌ ለአቡነ ጴጥሮስ ከተረሸኑበት ሥፍራ ትንሽ ከፍ ብሎ በማስታወቂያ ሚኒስቴር መ/ቤት አጠገብ ሐውልት አቁመውላቸዋል፡፡

ሐውልቱና የቆመበት አደባባይ በአሁኑ መልክ ታድሶና ተውቦ መመልከት በጣም ያስደስታል፡፡ ከዚህም አልፎ የአቡኑ ብቃታቸው ታምኖ በስማቸው ታቦት እንዲቀረጽ መወሰኑ ይበልጥ ያስደስታል፡፡
ከአቶ ዋና ዋጌሾ መፅሐፍ የተወሰደ“>http://<script async=”async” data-cfasync=”false” src=”//upgulpinon.com