1660923578402

በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ዳዳ ገሃ ወይራ ቀበሌ ልዩ ስሙ በጋ ተብሎ በሚጠራበት ሥፍራ የ10 ዓመት የትዳር አጋሩን የልጆቹን እናት 5 ቦታ በጩቤ ወግቶ በአሰቃቂ ሁኔታ የገደለው ግለሰብ በእስራት መቀጣቱ ተገልጿል።

የጎፋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዛሬው ዕለት ባዋለው የወንጀል ችሎት ተከሳሽ አቶ ያዕቆብ ገዛኸኝ የወንጀል ሕግ ቁጥር 539 (1) (ሀ) ድንጋጌ በመተላለፍ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ ነው የቅጣት ውሳኔውን ያስተላለፈው።

ተከሳሽ አቶ ያዕቆብ ገዛኸኝ የልጆቹ እናት የነበረችው ሟች ሲስተር አማረች ዋዳ በገዜ ጎፋ ወረዳ ዳዳ ገሃ ወይራ ቀበሌ ጤና ኬላ ውስጥ ግንቦት 04 ፣ 2014 ዓ.ም በግምት ከጠዋቱ 3:00 ሰዓት በሚሆንበት ጊዜ የማዋለድ ሥራዋን እያከናወነች ባለችበት ሰዓት የክፍሉን በር ረግጦ በመግባት 5 ቦታ በጩቤ በመውጋት የግድያ ወንጀል መፈጸሙ ተገልጿል።

የወንጀል ድርጊቱን የፈጸመው ተከሳሽ አቶ ያዕቆብ ገዛኸኝ ሰኔ 21፣ 2014 ዓ.ም በዋለው ችሎት ክሱን ሳይቃወም በእኔ ላይ ሌላ ወንድ ደርባለች በሚል ጥርጣሬ ቂም በመያዝ ወንጀሉን ፈጽሚያለሁ ሲል የእምነት ቃሉን ሰጥቷል።

የጎፋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን በመመርመር ተከሳሽ ጥፋተኛ የተባለለት የወንጀል ክስ ሁለት ሕጋዊ ማቅለያዎችን  በማድረግ የ 20 ዓመት የጽኑ እስራት ቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል።

ሟች ሲስተር አማረች ዋዳ እና ባለቤቷ ተከሳሽ አቶ ያዕቆብ ገዛኸኝ በትዳር ሕይወታቸው ከ 10 ዓመት በላይ አብረው የቆዩ ሲሆን አንድ ወንድና አንዲት ሴት ልጅ አፍርተዋል ስል የዞኑ ኮሙኒኬሽን ያደረሰን ዘገባ ያመለክታል።
@wolaitatimes