የበርካታ የማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት ነው የዎላይታ ብሔር። የብሔሩ የዘመን መለወጫ በዓል ”ጊፋታ” በየዓመቱ በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት መካከል አንዱ ነው፡፡ ጊፋታ የአዲስ ተስፋ ፍንጣቂ ተምሳሌት፣ የፍቅርና የአብሮነት መገለጫ እንዲሁም ወደ አዲስ ዓመት በአዲስ መንፈስ መሸጋገርን የሚያበስር ታላቅ በዓል ነው። የታሪክ ድርሳናት እንደሚያስረዱት ጊፋታ የዎላይታ ሕዝብ በኦሞ ወንዝ ተፋሰስ ቋሚ ኑሮ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ሲከበር የቆዬ ከማንኛውም እምነትም ሆነ የአምልኮ ሥርዓት ጋር ግኑኝነት የሌለው የዘመን መለወጫ ክብረ በዓል ነው፡፡

ለበዓሉ ታሪካዊ አመጣጥ ሁለት ዋና ዋና መላምቶች ይነገራሉ። የመጀመሪያው በወላይታ መንግሥት ተመስርቶ ግዛቱን ተቆጣጥሮ መኖር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ  በንጉስ “ካዎ ቢቶ” ዘመነ መንግስት ሲከበር እንደነበር የሚያስረዳ ሲሆን ሁለተኛው መላምት ደግሞ “በሞቼና ቦራጎ” ዋሻ እየተደረገ ካለው የአርኪዮሎጂ ጥናት ውጤት ጋር የሚያያዝ መሆኑ ይነገራል።

ጊፋታ በዎላይታ ብሔር ትልቅ ቦታ የሚሰጠው  ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ የብሔሩ የማንነት መገለጫ ነው።  የአሮጌው ዓመት ማብቅያና የአዲሱ ዓመት መጀመሪያ የመሸጋገሪያ በዓል ነው ጊፋታ። ጊፋታ  ታላቅ፣ መጀመሪያ፣ መሻገር እንደ ማለት ነው።  በዎላይታ ብሔር የዘመን አቆጣጠር ጊፋታ የዓመቱ የመጀመሪያ ወር ስያሜ ነው፡፡

እያንዳንዱ የማህበረሰብ አባል በጊፋታ በዓል ዝግጅት የየራሱ  የሥራ ድርሻ አለው። ሁሉም የቤተሰብ አባላት ሥራዎችን በዕድሜና በጾታ ተከፋፍሎ ይከውናል። የበዓሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራም በማህበር ወይም በደቦ ሆኖ አንዱ ሌላውን በማገዝም ይሰራል። በዓሉ ከሌሎች በዓላት በተለየ መልኩ የረጅም ጊዜ ቅድመ ዝግጅት ይደረግለታል፡፡ የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ዶክተር አበሻ ሽርኮ  የዎላይታ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል የሆነው ጊፋታ  ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፋይዳው የጎላ ነው ይላሉ።

በጊፋታ ዕለት ወንዶች በሬ ከታረደ በኋላ በታረደው በሬ ቆዳ ላይ ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ ይጀምራሉ፡፡ ዓመቱ ሲጠናቀቅ በተሰበሰበው ገንዘብ በሬ ከገዙ በኋላ የሚተርፈውን ገንዘብ ለቤት ውስጥ ወጪ ይጠቀማሉ፤ ለምግብነት የሚውሉ የምግብ ዓይነቶችን በዘር ወቅት መዝራት መሰብሰብና ለጊፋታ ወቅት ለይቶ ማስቀመጥ፤ ለማገዶ የሚሆኑ እንጨቶችን መሰብሰብ፣ በጊፋታ ወቅት ለከብቶች የሚሆን የሳር መኖ ማዘጋጀት፣ በዓሉ ሲቃረብ ለልጆች አዳዲስ ልብሶችን መግዛት፤ ለቅመማ ቅመም መግዣ የሚሆን ገንዘብ ለእናቶች መስጠት የአባዎራዎች ተግባር ነው።

የአካባቢ እድሳት ሥራም በአባወራዎችና በወንድ ልጆቻቸው የሚከናወን ተግባር ነው። አዲስ ዓመት የመታደስ ምልክት ነውና የመኖሪያ ቤቶች የሳር በአዲስ ይቀየራሉ፣ አዳዲስ የቤት ውስጥ መገልገያ እቃዎች ይገዛሉ በመኖሪያ ቤት ዙሪያና በአካባቢው የጽዳት ሥራዎች ይከናወናሉ።

የደለቡ በሬዎችን እና ሌሎች ለበዓሉ ድምቀት የሚያስፈልጉ ግብዓቶች የሚሸጡበት፣ የዕደ-ጥበብ ባለሙያዎች ስራቸውን ለገበያ የሚያቀርቡበት በዓል ነው ጊፋታ። በበዓሉ የእርድ እለት ለበዓሉ ቀደም ተብሎ በአባወራዎች የሚጀመር የቁጠባ  ባህል የዜጎችን የኢኮኖሚ አቅም የሚያጠናክር መሆኑን የገለጹት ዶክተር አበሻ፤ የቁጠባ ሥርዓቱ የ ጊፋታ በዓል ከተጠናቀቀ በኋላ በየሳምንቱ እስከ ምቀጥለው ዓመት የጊፋታ ገበያ ድረስ የሚቀጥል መሆኑን ያሰረዳሉ።

እናቶችም ከምግብ ቅቤ ጀምሮ በርካታ ግብዓቶችን ከጎረቤቶቻቸው ጋር በእቁብ በመቆጠብ በዓሉ ሲደርስ ለገበያ ያቀርባሉ። በሽያጭ የሚያገኙት ገቢም ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን ከፍ እያደረገ መሆኑን ያስረዳሉ። እንደ ወንዶቹ ሁሉ እናቶች ከበዓሉ በኋላ ለቀጣይ ዓመት በየሳምንቱ ቁጠባው በመቀጠል ከሰኔ ወር ጀምሮ ለቆጮ፣ ለሙቹዋ፣ ለባጪራና መሠል ባህላዊ ምግቦች የሚውል እንሰትን በህብረት በመፋቅ እንደሚያዘጋጁ አመልክተው ይሄም  የህብረት ስራን ከማጎልበት አንጻር ያለው ፋይዳ የላቀ መሆኑን አስረድተዋል።

ያለፈውን ዓመት የመንግስትና ስራ አፈፃፀም በህዝብ ዘንድ መገምገም ሌላው በጊፋታ በዓል የሚከናወን ተግባር ነው። ይሄም በሥራ እንቅስቃሴዎች ህዝቡ ያስተዋላቸውን ክፍተቶች የሚተችበትና የማስተካከያ ሀሳቦችን የሚሰጥበት፣ የተሻለ አፈጻጸም ያለው የሚበረታታበት ለአዲሱ ዓመት በአዲስ የስራ መንፈስ መነሳሳት የሚፈጠርበት ነው ብለዋል። ጊፋታ አዲሱን ዓመት በአዲስ ተስፋ በአዲስ መንፈስ መቀበልን የሚያበስር መሆኑን አመልክተው፤ በበዓሉ ላይ በህብረት የሚከናወኑ ተግባራት አብሮነትን በይበልጥ የሚያጠናክሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

አዲሱ ዓመት ሁል ጊዜ አዲስ ተስፋ ይዞ እንደሚመጣ ስለሚታመን በንጹህ መንፈስና በንጹህ አካል ለመቀበል በጊፋታ ዋዜማ እኩለ ሌሊት ላይ ሁሉም የማህበረሰቡ አባላት ከአሮጌው ዓመት እድፍና ቆሻሻ ጋር አዲሱን ዓመት አንቀበልም በሚል እምነት ውኃ አሙቀው ገላቸውን እንደሚታጠቡ ያስረዱት ደግሞ የዎላይታ ዞን የባህልና ቱሪዝም መምሪያ የባህል ታሪክና ቅርስ ስራ ሂደት ቡድን መሪ ከቶ አዳነ አይዛ ተናግረዋል። ይሄን የሚያደርጉትም አዲሱ ዓመት  በሽታ፣ ረሃብ፣ ድርቅ የሌለበት መልካም ዝናብ የሚዘንብበት፣ መልካም ነፋስ የሚነፍስበት፣ የጥጋብ ዓመት እንዲሆን ካለፈው ዓመት ኃጥያት መንጻት አለብን ተብሎ ስለሚታመን መሆኑን አስረድተዋል።

 ሐሬ ሀይቆ፣ ቦቦዶ፣ ጎሻ  እና ‘ቃኤ ጊያ የ ጊፋታ  በዓል መቃረቡን የሚያበስሩ  በእንቅስቃሴያቸው ከወትሮ የተለዩ የገበያ ቀናት መሆናቸውን አብራርተዋል። ወቅቱ በህብረተሰቡ የጊፋታ በዓል ዝግጅት ሸመታና ሽያጭ የሚጀመርበት መሆኑን አምልክተው፤ የገበያ ቀናቱ አልባሳት፣ ቅቤ፣ ሠንጋ በሬ፣ ጌጣ ጌጦች፣ የስፌት፣ የሸክላ፣ የብረታ ብረት ምርቶችና የተለያዩ ለምግብነት የሚውሉ ግብአቶች የሚገዛባቸውና የሚሸጥባቸው እጅጉን የደሩ የገበያ ቀናት መሆናቸውን አስረድተዋል። ማህበረሰቡ የተለያዩ የባህላዊ ምግቦችን፣ ዳታ በርበሬ፣ ቦርዴ፣ጠላ፣ ጠጅ፣ቃሬቦ እና ወተት መጠጦችን በትልቅ እንስራ በማዘጋጀት የፍቅር ማዕድ በጋራ ይመገባሉ።

ወጣት ወንዶች “ጉሊያ” ለሚሰኘው የደመራ ዝግጅት እንጨት ከመቁረጥና ከማቆም ጀምሮ የከብቶችን ሣር በማጨድና በመከመር፣ እንጨት በመፍለጥ ለበዓሉ ጊዜ ከማስቀመጥ አልፎ ከዘር እና ከአጨዳ ወቅት ጀምሮ ሁሉንም የጊፋታ ዝግጅት ስራዎችን በጊዜ በመከፋፈል ያከናውናሉ።

የዎላይታ ዞን የሀገር ሽማግሌ አቶ አብርሃም ባቾሬ በበኩላቸው ጊፋታ የእርቅ፣ የሰላምና የአንድነት መገለጫ በዓል መሆኑን ይናገራሉ። ጊፋታ የተጣሉ ባለትዳሮች፣ ቤተሰቦች፣ ጎረቤቶች እንዲሁም የአካባቢው ሰው የሚታረቅበት ወቅት ሲሆን አዲስ ጎጆ ለመቀለስ የተጫጩም ለቤተሰብ የሚያሳውቁበትና ሶስት ጉልቻ የሚመሰርቱበትም ጭምር ነው።

በጊፋታ ጥላቻና ቂም ስፍራ የላቸውም ያሉት የሀገር ሽማግሌው ረጅም ጊዜ ሳይከፈል የቀረ ዕዳም ቢኖር በጊፋታ ለባለቤቱ ይመለሳል ብለዋል። በበዓሉ በተለያየ ምክንያት ከአካባቢው ርቀው የቆዩ ሰዎች ወደ ቀያቸው የሚመለሱበትና አዲሱን ዓመት በፍቅር በደስታ በአንድነት የሚቀበሉበት በዓል መሆኑን አስረድተዋል።

የጊፋታ በዓል ከመስከረም 14 እስከ 20 ድረስ ባሉ ቀናት በሚውለው እሑድ ቀን የሚከበር መሆኑን አመልክተው ከበዓሉ በፊት ያሉት የሐሙስ የአርብና ቅዳሜ ቀናት የራሳቸው ባህላዊ እሴት ያላቸው የስራ ቀናት መሆናቸውን አስረድተዋል። እነዚህም “ኮሴታ ሃሙሳ” ፣ “ሱልኣ አርባ”ና “ባጪራ ቄራ” የሚል ስያሜ ያላቸው ናቸው ብለዋል።በነዚህ ቀናት ለቦርዴ የሚሆን እህል፣ ለሆድ ማሟሻ ጎዳሬ (Boynaa Cadhdhiyaa)ና ከቦዬ የሚዘጋጅ (Boyyiaa Pichaata)፣ ባጪራ፣ ሙቹዋ፣ ጉርዱዋ የሚዘጋጅባቸው መሆናቸውን አብራርተዋል።

የጊፋታ በዓል ጎረቤትና ዘመድ አዝማድ የሚሰባሰብበት፣ ፍቅራቸውን ከአንድ ማዕድ በመቁረስ የሚያድሱበት ለበዓሉ ከተዘጋጀው መጠጥ የፍቅር መግለጫ በሆነው የ”ዳጌታ” ሥርዓት የሚጠጣበት ሰላምና ፍቅር የሚሰፍንበትና አዲስ ተስፋ የሚፈነጥቅበት የአዲስ ዓመት ማብሰሪያ ነው።

እንደ አቶ አብርሃም ገለፃ ከጊፋታ ቀጥሎ የሚመጣው ሁለተኛው ቀን ማክሰኞ “ጪሻ ማስቃይኖ” የሚሰኝ ሲሆን ሰዎች የመልካም ምኞት አበባ ስጦታዎችን የሚለዋወጡበት ቀን ነው፡፡ በጊፋታ ወቅት የሚፈኩ አበቦችን ሲቀበሉ ካመት ዓመት ድረስ “ጊፋታ”ን እናንተ ቆጥራችሁ አክብሩት እንጂ ጊፋታ አይቁጠራችሁ “Gifaatay Inttena Qoodoppo Initte Gifaataa Qoodite” በማለት ይመራረቃሉ።

እንዲህ እንዲህ እያለ የጊፋታ በዓል መገባደጃው ይደርስና ከበዓሉ ጋር ተያይዞ በነበረው የመዝናኛ ወቅት ሰዎች ከስራ እንዳይዘናጉ ሁሉም ችቦ እያቀጣጠለ ለሚመጣው በዓል አምላክ በሰላም እንዲያደርሰው በመመኘት ጊፋታን ይሸኛል፡፡

የጊፋታ በዓል ለአብሮነትና ለሰላም እንዲሁም የስራ ባህልን ጠንካራ ለማድረግና ግብረ ገብነት ለማጎናጸፍ ያለው ፋይዳው የጎላ መሆኑን የተናገሩት አቶ አብርሃም በተለይም ዜጎች ነገን በተስፋ በማየት ለስኬት እንዲበቁ ከማድረግ አንጻር ያለው ተፈጥሮአዊ አቅም ወሳኝ ነው ብለዋል። በመሆኑም እነዚህ ቱባ ባህሎቻችንን በአግባቡ  በመጠቀምና ለትውልድ በማሻገር የሀገርን ከፍታ ማረጋገጥ እንደሚገባ አመላክተዋል ስል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *