

“በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተው ጦርነት ወደ መቋጫ እየተቃረበ በመሆኑ በጦርነቱ ያሳየነው ድል በሠላም እንዲደገም መስራት ይኖርብናል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በዛሬው ዕለት የጎፋ ዞን ጉብኝት አድርገዋል።

የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶ/ር ጌትነት በጋሻው የእንኳን በደህና መጣችሁ መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት በጎፋ ዞን የጎፋ እና ኦይዳ ብሔረሰቦች እንዲሁም በርካታ የሀገራችን ብሔር ብሔረሰቦች፣ በድምሩ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ የሚገመቱ ሕዝቦች ተዋልደውና ተጋምደው፣ በመተሳሰብና በፍቅር፣ በአብሮነትና በሠላም የሚኖሩበት መሆኑን ተናግረዋል።

ዞኑ የኢትዮጵያዊነት ተምሳሌት የሆነ፣ ምድሩ ለምለም፣ እምቅ የተፈጥሮና የእንስሳት ሀብት፣ የበርካታ ተፈጥሯዊና ባህላዊ መስህቦች ባለቤት መሆኑን አስገንዝበዋል።
የጎፋ ሕዝቦች የዘመናት ጥያቄ የነበረው በዞን መዋቅር የመደራጀት ጥያቄ ምላሽ ያገኘው ከሀገራዊ ለውጡ ማግስት መሆኑን ገልጸው፣ የጎፋ ዞን መዋቅር ከሀገራዊ ለውጡ ትሩፋቶች መካከል አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።
የሶዶ-ዲንኬ- ሣውላ- ሸፍቴ የኮንክሪት አስፓልት መንገድ ጥያቄ በሀገራዊ ለውጡ ማግስት ምላሽ አግቶ እየተሰራ እንደሚገኝ የገለጹት ዶ/ር ጌትነት፣ ለዚህም የለውጡ መሪያችንን እጅግ አድርገን እናመሰግናለን፣ እናደንቃለን ብለዋል።
ሆኖም በአሁኑ ሰዓት የመንገዱ ግንባታ መሠረታዊ እንቅፋቶች ገጥሞታል ያሉት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ፣ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ፕሮጀክትን በመጀመር ብቻ ሳይሆን በማጠናቀቅ በምታወቁበት ልዩ የአመራር ጥበብ ለዚህ መንገድ ጉዳይ መፍትሔ እንደሚያበጁ ሙሉ እምነት አለን ሲሉ ጠይቀዋል።

ዋና አስተዳዳሪው አክለውም ከሀገራዊ ለውጡ ማግስት ጀምሮ ፍትሐዊ ምላሽ የጀመሩት የዞናችን ሕዝቦች ለውጡ ከፍተኛ ስሜትና ቦታ አላቸው፣ ለውጡን በሙሉ አቅማቸውና ሀሳባቸው ይደግፋሉ ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ባስተላለፉት መልዕክት የጎፋ ዞን ከዎላይታ፣ ከጋሞ ዞን፣ ከዳውሮ ዞን፣ ከጂንካ እና ከሌሎች አጎራባች አካባቢዎች ጋር በማስተሳሰር የጎፋ ዞን የብልጽግና ማዕከል እንዲሆን መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የአልባ እና የወይላ ተራራዎች የጎፋ ዞን ሕዝቦች ከፍታ የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል።

የጎፋ ዞን ሕዝቦች ከውስጥና ከውጭ የሚያጋጥሙ ወረራዎችን በመመከት ከሌሎች ወንድም ኢትዮጵያን ጋር በመሆን የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ለማስከበር ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈሉ ሕዝቦች ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተው ጦርነት ወደ መቋጫ እየተቃረበ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ፣ በጦርነቱ ያሳየነው ድል በሠላም እንዲደገም መስራት ይኖርብናል ሲሉ ተናግረዋል።