

በዩኒቨርሲቲው የSTEM ማዕከል ተማሪ የሆነችው ተማሪ ሳሮን ቡሳ በፈጠራ ሥራ ውድድር በአንደኝነት አሸንፋለች።
ለ7ኛ ጊዜ የሚከበረውን አለም አቀፍ የሳይንስ ቀን አስመልክቶ በተማሪዎችና መምህራን «ሀገራዊ የፈጠራ ስራ ውድድር» ተካሂዷል።
ውድድሩ በትምህርት ሚኒስቴርና አጋር ድርጅቶች ትብብር ከጥቅም 27- ህዳር 2/2015 ዓ/ም በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል።
በተካሄደው ሀገራዊ የፈጠራ ስራ ውድድር የተሳተፈው የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ STEM ማዕከልም 1ኛ ደረጃ በመውጣት አሸናፊ ሆኖ የምስክር ወረቀት ተበርክቶለታል።

የዩኒቨርሲቲውን STEM ማዕከል በመወከል በሳይንስና ኢንጂነሪንግ የፈጠራ ሥራ ውድድር የተሳተፈችው ተማሪ ሳሮን ቡሳ፤ ከቀረቡ 195 ፕሮጀክቶች መካከል በኢንጅነሪንግ ዘርፍ በአንደኝነት አሸንፋለች።
በዘርፉ በአንደኝነት ላሸነፈችው ተማሪ ሳሮን ማበረታቻ እንዲሆን በአዘጋጆቹ የትምህርት ሚኒስቴር እና አጋር ድርጅቶች የላፕቶፕ ሽልማት ተበርክቶላታል።
በዉድድሩ የላቀ ተሳትፎ ላደረጉት የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ STEM ማዕከል የላቦራቶሪ ኤክስፐርት በረከት ጌታቸዉ ደግሞ ዋንጫ ተሸልመዋል።
በዩኒቨርሲቲው ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዚዳንት የሆኑት ዶ/ር መስፍን ቢቢሶ የምርምርና የፈጠራ ስራዎችን አጠናክረን በመስራት የማህበረሰባችንን ችግር መቅረፍ አለበን ብለዋል፡፡
ለተገኘው መልካም ውጤት የማዕከሉ የሥራ ሃላፊዎችን እና ተሸላሚዎችን ምክትል ፕሬዝዳንቱ አመስግነዋል።
የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የዩኒቨርሲቲ – ኢንዱስትሪ ትስስር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ዉብአለም ግርማ በበኩላቸው ምንም እንኳን ማዕከሉ ስራዉን በጀመረ በቅርብ ጊዜ ውስጥ በፈጠራ ስራ ዉጤት ማምጣት መጀመሩ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ገልጸዋል።

ለተገኘው ውጤት አጠቃላይ የዩኒቨርሲቲውን ማህበረሰብ “እንኳን ደስ አላችሁ!” በማለትም ዶ/ር ውብዓለም ደስታቸውን አብስረዋል ስል የዩኒቨርሲቲው ኮሙኒኬሽን ያደረሰን ዘገባ ያመለክታል።