በዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕረሄሲቪ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሀይል ጥቃት የደረሰባቸውን የህክምናና የህግ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል ማዕከል ተከፈተ

በሆስቲታሉ የአንድ ማእከል የፍትህ አገልግሎት መስጫ ተመርቆ ለአገልግሎት ማስጀመሪያ መርሀ ግብር ላይ እንደተገለፀው በሴቶች እና ህፃናት ላይ ፆታዊ ጥቃት ሲደርስ የቃል መቀበልና የክስ ሂደትን ለማቀላጠፍ እንደሚያስችል ታውቋል።

የፆታ ተኮር የሀይል ጥቃት የደረሰባቸውን በአንድ ማእከል የህክምና እንዲሁም የህግ አገልግሎት እንዲያገኙ እንደሚያስችል በዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕሪሄንስቪ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የመስክ ምልከታ ባደረጉበት ወቅት የዞኑ ፍትህ መምሪያ ሀላፊ አቶ እንዳሻው አባተ አብራርተዋል።

አቶ እንዳሻው አክለውም ፍትህ፣ ፖሊስ ፣ ሴቶችና ህጻናት እና ጽ/ቤቶች የአንድ ማእከሉን ስራ እንዲደግፉ አሳስበዋል።

የዎላይታ ሶዶ ከተማ ፍትህ ፅህፈት ቤት እንዲሁም ከፓሊስ ፅህፈት ቤት በጋራ በመሆን ስራዉን በማዕከሉ የሚያከናውኑ አካላትን በቋሚነት መድበዋል።

የተመደበዉ ዓቃቤ-ህግና መርማሪ ፖሊስ የሚመጡ ጉዳዮችን ከህክምና ባለሙያዎች ጋር በመቀናጀት ጥልቀት ያለዉ ምርመራ በማከናወን ጉዳዩን ለማየት ሥልጣን ላለዉ ፍ/ቤት በማቅረብ ፍትህን እንድያረጋግጡ የጋራ ሀላፊነት መቀበላቸውን በመስክ ምልከታው ወቅት ተገልጿል።

በዩኒቨርስቲው ምክትል ፕሬዘዳንት የሆኑት ዶክተር ሙላቱ ዴአ የአንድ ማእከል አገልግሎቱን ለማጠናከር የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ አስረድተዋል።

የህክምና እንዲሁም የስነልቦና ድጋፍ የሚያደርጉ የዘርፉ ባለሙያዎችን በመመደብ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት በቅንጅት እንደሚሰራም ዶክተር ሙላቱ አብራርተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *