
ላለፉት ስድስት አመታት ጀምሮ መንግስት በዎላይታ የሚጀመረውን እንጂ የሚጨርሰውን ልማት ለምን ማየት አልተቻለም ? መንግስት በዎላይታ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ከሕዝቡ ፖለቲካዊ ምክንያቶችና ከመልማት ፍላጎቱ ጋር በፍጹም የሚጣጣም አለመሆኑ ለምን ይሁን ? ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባይጠሩም አዲሱ ፕሬዘዳንት ታዬ አስቀስላሴ የዎላይታ ሶዶን ስም በአንደኛ የጠሩት በባለፈው ቅሬታ ይሁን ? እና በሌሎች እንደወትሮው ሁሉ የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ የሆኑት ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና በዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ለተነሱ ጉዳዮች ምላሽ ሰጥተዋል፥ ዘገባውም ቀጥታ እንደሚከተለው ቀርቧል።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ ከሌዊ እስከ ግብርና ኮሌጅ ይገነባል ተብሎ የዉሃ ሽታ ስለሆነዉ የአስፋልት መንገድ ጉዳይ ሐሳቦትን ቢያጋሩን?
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ አዎ ሁሌ የሚያንገበግበኝን ጉዳይ ነዉ ያነሳሄዉ። በዎላይታ ሶዶ እንደ ዋና ጎዳና የሚታየዉ ከሌዊ እስከ ግብርና ኮሌጅ የሚዘልቀዉና ከዛም በዩኒቨርስቲው በር አድርጎ የሚዘልቀዉ መንገድ ነው። ለዘመናት ሕዝቡ ደረጃዉን ጠብቆ እንዲሰራ ሲጠይቅ ከርሞ ከቅርብ አመታት ወዲህ በተደጋጋሚ ይጀመራል ተብሎ ሲጓተት ከርሞ አምና ዲዛይኑ ሳይቀር በዎላይታ ቴሌብዥን ከመተላለፉ በተጨማሪ የተለዋጭ መንገድ ዝግጅት መደረጉም ተዘግቦ እንደነበረ ይታወሳል።
አሁንም በተግባር ግን ምንም የተጀመረ ነገር የለም። አንዴ በመንገዱ የሚገኝ አንድ ተቋም መነሳት የሚገባቸዉን ሱቆች ለማንሳት ካሳ ተከፍሎም ዳተኝነት በማሳየቱ ነው የተስተጓጎለዉ የሚሉ ጭምጭምታዎች ነበሩ። አሁን ደግሞ የተለያዩ የመንግስት አካላት የዉሃ እና የመብራት መስመሮች የማንሳት ጉዳይ ያንተ ነው፣ ያንተነዉ እየተባባሉ መስማማት ባለመቻላቸው ተስተጓጉሏል ተብሎ በሕዝቡ ዘንድ ይወራል።
በግሌ ተጨባጭ ምክንያቱን ባላዉቅም መንገዱ ባለመሠራቱ የከተማዋ ሁለንተናዊ ልማት እየተስተጓጎለ ነው። በእዉነቱ አሁን መንገዱ ያለበት ደረጃ ከተማዋን ካለመመጠኑም በተጨማሪ አሳፋሪ ነው። መንገዱ ተሠርቶ ማለቅ በነበረበት በዚህ ሰዓት ስለአለመጀመሩ ማዉራት በጣም ያሳዝናል። በየደረጃው ያለዉ አመራር ይህ ጉዳይ ሊያንገበግበዉ ይገባል።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ ምናልባት ከቦዲቲ በሌዊ በኩል የሚያስገባዉ መንገድ ዳልቦ ላይ ከተዘጋ ቆይቷል፣ እሱስ መንገድ ካነሳነዉ መንገድ ጋር የተያያዘ ይሁን በአጠቃላይ በዎላይታ የአዳዲስ ፕሮጀክቶች በበቂ ሁኔታ አለመኖርና ቃል የተገቡቱም ከሌሎች አካባቢዎች በተለዬ ሁኔታ መስተጓጎላቸዉን እንዴት ያዩታል?
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ አዎ በተጨባጭ የሚታዩ ችግሮችን ነው ያነሳው። የጠቀስከዉ መንገድ መዘጋቱን እንጂ ስለመጀመሩም ይሁን ከጠቀስነዉ መንገድ ጋር የዲዛይን ማሻሻያ ተደርጎ አብሮ ሊሰራ ስለመሆን አለመሆኑ መረጃዉ የለኝም።
ይህ መንግስት ለዉጡ አስፈልጓል ብሎ ከሚሰጣቸዉ ምክንያቶች አንዱ ፕሮጀክቶች በጊዜ አለማለቃቸዉ ነው ብሎ ሲያበቃ፤ በዎላይታ ግን የአየር ማረፊያዉንና የጠቀስነዉን መንገድ መስተጓጎል አይነት ነገር ከለዉጡ በፊት አልነበረም ማለት ይቻላል። በጣም ግራ የሚያጋባ ነው። በዎላይታ የሚደረገዉ እንቅስቃሴ ከሕዝቡ ፖለቲካዊ ምክንያቶች እና ከመልማት ፍላጎቱ ጋር በፍጹም የሚጣጣም አይደለም።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባይጠሩም ፕሬዘዳንት ታዬ አስቀስላሴ የዎላይታ ሶዶን ስም በአንደኛ ጠርተዉ በአዲስ አበባ የተጀመረዉ ኮሪደር ልማት እንደሚቀጥልባት አስታዉቀዋል። በአሁኑ ሰዓት ለዚህ ዝግጁ የሆነ መንገድ ከተማዋ ያላት ይመስልዎታል?
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ በብዛት አላት ግን የአጭርነትና የ topographic ችግሮች የሚስተዋልባቸዉ ይመስለኛል። በጣም ጥሩ የሚሆነዉ ግን ይሄዉ የሌዊ ግብርና ኮሌጅ መንገድ ተሰርቶ የሳይክልና የእግረኛ መሄጃ ቢሰራለት የበለጠ ጥሩ ይመስለኛል። ለዚህ ተብሎ ግን ቀድሞ በወጣዉ ዲዛይን ላይ የነበረዉ የመንገድ ስፋት ወይንም የ lane ብዛት መቀነስ የለበትም።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ አሁን ለዚህ ወሳኝ መንገድ ግምባታ ማን ምን ያድርግ?
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ ይህ በወሳኝ ጀረጃ የከተማዋን ገጽታ የሚቀይር መንገድ ነዉና ባለድርሻ አካላት ሥራቸዉን በአግባቡ መሥራት አለባቸዉ። ሕዝቡም በየመድረኩ መወትወት አለበት። በተለይ በመንገዱ የሚገኙ ተቋማትና ግለሰቦች መነሳት ያለበት ንብረት ካላቸዉ ልማቱ የነሱም ነውና ተባባሪ መሆን አለባቸዉ።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ በግምባታዉ ሂደት መወሰድ ያለባቸዉ ጥንቃቄዎች ካሉ አንስተን ብንቋጭስ?
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እሺ ጥሩ። መንገዱ ብዙ የተለያዩ አይነትና ደረጃ ያላቸዉ መጋቢ መንገዶች የሚገናኙት ስለሆነ በተቻለ መጠን ሌላ ተጨማሪ ወጪ እንዳይበዛ ከመንገዶቹ ጋር ከፍና ዝቅ እንዳይል ጥንቃቄ ይፈልጋል።
ሌላዉ ወደፊት የሚለሙ የታጠሩ ቦታዎችና አሮጌ ቤቶች ጉዳይ ብዙ ባያስጨንቅም በተለይ አሁን ላይ የተገነቡ ተቋማትና ሕንጻዎች በተጋነነ ሁኔታ እንዳይሰቀሉ፣ አልያም እንዳይቀበሩ በተቻለ መጠን ጥንቃቄ ቢደረግ እላለሁ።
ከዛ በተረፈ በአንዴ ሁሉንም መቆፈር ስለማያስፈልግ በደምብ ተጠንቶ በሁለት ወይንም በሶስት ቦታ ተከፍሎ መንገዱ ቢሰራ ችግር ያለዉ አይመስለኝም። መንገዱ ሲያልቅ ከግብርና ኮሌጅ በዩኒቨረስቲ አድርግ እስከ ሁምቦ መዉጫ ወደፊት በተመሳሳይ ስፋት መቀጠል ያለበት ይመስለኛል።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ እንደወትሮው ሁሉ ፈቃደኝነት አሳይተው በተነሱ ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ማብራሪያና ትንታኔ ስለሰጡን በሚዲያችን እንዲሁም በውድ ተከታዮቻችን ስም እናመሰግናለን።
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እኔም አመሰግናለሁ።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ መልካም። ዳግም በሌላ ጉዳይ እንደምንገናኝ ተስፋ እናደርጋለን።
ማሳሰቢያ ለውድ አንባቢያን፦ የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በዚሁ “የፖለቲካ ወጌሻ” መደበኛ እንግዳ ዝግጅት ጠለቅ ያለ ልምድና ክህሎት ካለው ፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ በፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና ( የብዕር ስም ) ጋር ቆይታ በማድረግ ያቀረበ ሲሆን ከዚህ በፊትም በተለያዩ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች እንዳቀረብነው የሚታወስ ነው። በቀጣይም በሌሎች ጉዳዮች እንደምንመለስ በአክብሮት እንገልፃለን።
WolaitaTimes , በህብረተሰብ ውስጥ🙏 ስለአብሮነታችሁ እናመሰግናለን🙏 #Ethiopia #Wolaita #Tigray #Amhara #Oromia #addisababa
በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ ቃለመጠየቅ ተደርጎ የተዘጋጀ ዘገባ ነው