በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ እና በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈሪ አባቴ የሚመራ አሳዛኝና ጫፍ የወጣ የሙስና ቅሌትና የሌብነት ሰንሰለት መዘርጋቱን WT Media ከውስጥ ምንጮች ባገኘው ዝርዝር ሰነድ መረጃ አረጋግጧል።
ይህ ሰንሰለት የሕንፃ ግንባታን፣ የሕገወጥ ቅጥሩን፣ የፋይናንስ ብልሹነትን እና የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን የማጥቃት ዘመቻን ያካተተ መሆኑ ተጠቁሟል።
- የርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት ሕንፃ ግንባታ ቅሌት: 200 ሚሊዮን ብር ያለ ጨረታ
እንደ መረጃው ከሆነ፣ የፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ሕንፃ ግንባታ ሥራ ከመንግሥት ፋይናንስ ሥርዓት ውጭ በሆነ መንገድ፣ ያለ ምንም ጨረታ ለአንድ አትም ኮንስትራክሽን በድርድር መሰጠቱ የሙስናው ማዕከል ነው።
አቶ ጥላሁን ከበደ በቀጭን ትዕዛዝ ሥራ ተቋራጩ ወደ ሥራ እንዲገባ ካደረጉ በኋላ፣ ለመስተዳድር ምክር ቤትና ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዱፄ ታምሩ ፊርማ ወጥቶ 200 ሚሊዮን ብር ለቅድመ ክፍያ ወደ ሥራ ተቋራጭ ድርጅት አካውንት ተዘዋውሯል።
አቶ ጥላሁን እና አቶ ተፈሪ አባቴ በመመሳጠር፣ የተዘዋወረውን ገንዘብ ለግል ጥቅማቸው ለማዋል በማቀናበር፣ የኮንስትራክሽን ባለሀብቱን በስልክ በመጥራት “አጭርና ቀጭን ተጨማሪ ክፍያ እንድትጠይቅ” የሚል መላክ ተሰጥቶታል።
የክፍያ ሁኔታው “እጅግ በጣም ሚስጥራዊ” ነው በማለት፣ ከመዝገብ ቤት ውጭ የፕሬዝዳንቱ የወንድም ልጅ በሆኑት አቶ ባህሩ ሙሉቱ አማካኝነት ክብ ማኅተም በማስደረግና የሐሰት ደብዳቤ ቁጥር በመስጠት፣ የጥቅም ተጋሪዎች ብቻ በሆኑ ግለሰቦች ልዩ ኮሚቴ ተቋቁሞ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ተጨማሪ ገንዘብ ለማጭበርበር ከስምምነት ተደርሷል።
- በዘመድ አዝማድ የተደራጀ የሌብነትና የኃላፊነት ብልሹነት
የርዕሰ መስተዳድሩ ጽ/ቤት በአንድ ብሔርና በአብሮ አደግ በሚል ስብስብ ውስጥ መሆኑ ለዚህ ሁሉ ሕገወጥነትና ሌብነት መሳካት ዋና ምክንያት እንደሆነ WT Media ባደረገው ዳሰሳ ምርመራ ዘገባ ለማረጋገጥ ችሏል።
በዚህም፦ አቶ ባህሩ ሙሉቱ: (በካቢኔ ማዕረግ የፕሬዝዳንቱ ፕሮቶኮልና የመንግሥታት ግንኙነት ኃላፊ) የፕሬዝዳንቱ የወንድም ልጅ ናቸው።
አቶ ዱፄ ታምሩ: (በካቢኔ ማዕረግ የርዕሰ መስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ) ለፕሬዝዳንቱ በእናቱ በኩል የቅርብ ዘመድ ናቸው።
ዶ/ር ቦሻ ቦምቤ: (በካቢኔ ማዕረግ የፕሬዝዳንቱ ልዩ አማካሪ) አብሮ አደግ ሲሆኑ ተቋሙን እንደ “መንግሥታዊ ተቋም ሳይሆን ቤተሰባዊ” አድርገውታል።
የጽ/ቤቱ ዝርፊያ: አቶ ባህሩ ሙሉቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ያለምንም ስብሰባ ከአርባ ምንጭ ሆቴሎችና ሎጆች “የአልጋ ወጪ” በማለት በሕጋዊ ደረሰኝ እየዘረፉ ይገኛሉ። እንዲሁም ለግል ጉዳይ በስራ ማስኬጃ ሽፋን ከፋይናንስ ሕግ ውጭ ወጪ ያደርጋሉ።
መረጃ እንዳይወጣ የረጅም ጊዜ ባለሙያዎችን በማውጣት፣ በአዋጅ ታግዶ ሳለ አዲስ ቅጥርና ዝውውር ከጋሞና ጎፋ ዞን በማድረግ የመንግሥት ተቋማትን እያተራመሱ ነው። ለምሳሌ የሰው ሀብት ሥራ ሂደት አመራር የነበረውን በማስጨነቅ ሥራ እንዲለቅ ካደረጉ በኋላ፣ አቶ ጥላሁንን ከዚህ ቀደም የኮሌጅ አመራር ሲያጠቁ የቆዩ ግለሰብን ‘ለዚያ ውለታ’ ሕገወጥ ቅጥርና ዝውውሩ ምቹ እንዲሆን የሰው ኃይል ኃላፊ አድርገው ሾመዋል።
የጉልበት ብዝበዛ: በኮንትራት ተቀጥረው ለዓመታት የሰሩ ታች ሠራተኞችን ከቢሮ በማባረር፣ እንዲሁም መንግሥት የጨመረውን ደመወዝ በመከልከል የቀድሞ 1100 ብር ብቻ እየከፈሉ ጉልበት ብዝበዛ እየፈጸሙ ነው።
- የማዕድን ክስና የፖለቲካ ተቃዋሚዎች ስደት
የክልሉ አመራሮች በሕገወጥ መንገድ የሚካሄዱ የማዕድን ቁማር ሥራዎችን ሕጋዊ ለማስመሰል ከተለያዩ ተቋማት የሚመለከታቸውን ሰዎች በማዋቀርና ሰነድ በማደራጀት፣ በልማታዊ ባለሀብት በኢንጂነር ብርሃነመስቀል ክንፈን ህግን ባልተከተለ ሁኔታ ካሰሩ በኃላ ክስ መጀመሩን WT Media በተደጋጋሚ ከዚህ ቀደም ዘግቧል።
ይህንን ክስ እንዲመራ ለረጅም ዓመታት በወንጀል ምርመራ ዕውቀት የነበራቸው ረዳት ኮሚሽነር ሲሳይ (ዎላይታ ናቸው በማለት) ከሥልጣን በማንሳት፣ በአብሮ አደግነት ዝቅ ያለ ማዕረግ ያለው ኮማንደር ጉራማይሌ በማስቀመጥ ከፌዴራል ለሚመጡ መርማሪዎች የተዛባ መረጃ እንዲሰጥ በማድረግ ንጹህ ባለሀብቱን እያሰቃዩ ይገኛሉ።
አቶ ባህሩ ሙሉቱ የፕሬዝዳንቱ ሥምና ፊርማ የተቀረጸበትን ክብ ማኅተም ይዘው በመዞር፣ በሄዱበት ሁሉ ሕገወጥ ሥራዎችንና የወንጀል አሻራቸውን እያኖሩ ቀጥለዋል።
በመሆኑም በተለይም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ እና በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈሪ አባቴ የሚመራው ቡድን ከላይ የተጠቀሱ ግለሰቦችን ተጠቅሞ የመንግሥትና የህዝብ ሀብት የመዘበሩበትና ለመመዝበር የተጠቀሙበት የሰነድ መረጃዎች፣ የስልክ ጥሪዎችና መልዕክቶች ለWT Media ከውስጥ ምንጮች የደረሱ ቢሆንም የሚመለከታቸው አካላት ጉዳዩን ለማጣራት የሚያደርጉትን ምርመራ ሂደት ሊያደናቅፍ ይችላልና ለጊዜው ይፋ አናወጣም።
ማሳሰቢያ፦ WT MEDIA በሀገሪቱ በተለይም ደቡብ ኢትዮጵያ አከባቢ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት በማያገኙ ለተጮቆኑ ህብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥተው እውነትንና ሀቅን መሠረት አድርገው የሚሰራ ስለሆነ የመረጃ ሰጪ ግለሰቦች ምስጥርና ደህንነት በተጠበቀ ሁኔታ የደረሱን መረጃዎችን መልሰን አጣርተን ለህዝብና የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡበት በታማኝነት ይፋ እናደርጋለን።
ለማህበረሰቡ ከፍተኛ ፋይዳ ባላቸው ህዝብ ጉዳዮች ላይ ሀሳባችሁን ለማካፈል ለሚፈልጉ ሁሉ ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ሆነን እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚፀባረቅበት በሌሎች ትላልቅ ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለ ዘውትር አብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው!! እኛ ዘውትር የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን !!
Voice of Marginalized Community – WT Media