በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አንዲት ወጣት ሴት በማኅበራዊ ሚዲያ የማልበርግ ቫይረስን የመከላከል ክፍተትን በመተቸቷ ዋስ መብቷንም ጭምር ተከልክላ ከሁለት ሳምንት በላይ በእስር ላይ እንደምትገኝ ቤተሰቦቿና የቅርብ ጓደኞቿ ተናግረዋል።
የደቡብ ኦሞ ዞን ነዋሪ የሆነችውና በማኅበራዊ ሚዲያ “ፍሬ ሐመር ቱርሚ” በሚል ስም የምትታወቀው ወጣት ሴት፣ በዞኑ ውስጥ የማልበርግ ቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ የአካባቢውና የክልሉ መንግሥት ያሳዩትን ክፍተት በመተቸቷ ወደ እስር መላኳ ተገልጿል።
WT Media ከቤተሰቦቿና ከቅርብ በጓደኞቿ ባገኘው መረጃ መሠረት፣ ፍሬ ሐመር ቱርሚ በደቡብ ዞን ፖሊስ ዲማካ ታስራ ያለማንም ጠያቂና ያለዋስትና መብት ተከልክላ ፍርድ ቤት ሳትቀርብ ከሁለት ሳምንት በላይ ሆኗታል።
እንደ ቅርብ ጓደኞቿ ገለፃ የእስሩ መንስኤ “እውነትን በመናገሯ ብቻ በማሰር እየተንገላታች ያለችው ፍሬ፣ የጤና ባለሙያ፣ የማኅበረሰቡንና የቤተክርስቲያንን ጉዳይ በአቅሟ ልክ በመርዳት የምትታወቅ ብርቱ ሴት ናት። ወደ እስር የተላከችው፣ በማኅበራዊ ሚዲያ የዞኑንና የክልሉን ጤና ቢሮ ድክመቶች በግልጽ በመተቸቷ ነው”።

ከ12 ቀናት በፊት (November 29, 2025) በግል የፌስቡክ ገጿ ያጋራቻቸው ቁልፍ ትችቶች የሚከተሉት እንደሆነ WT Media ተመልክቷል።
የእርዳታ ግብዓቶች አያያዝ ጥያቄ በተመለከተ: “እሽ የት ነው ያለው??? የት የት ታደለ?? ሚዲያ ላይ በቪዲዮም በፎቶም ሲሰጥ የነበረው የርክክብ ሂደት እንየው አሳዩን። ግብዓቶችም፣ መኪናዎችም የት የት እየተሰጠ እና አገልግሎት እየሰጡ እንደሆነ ማወቅ እንፈልጋለን።” በማለት በሕዝብ ስም የተሰጠው እርዳታ አያያዝ ላይ ያለመተማመንን ገልጻለች።
የመግለጫ መዘግየትን ደግሞ “ሁሉም ጩኸት ከበዛ በኃላ የተሰጠ መግለጫ ነው። ዝም ቢባል ዝም ሊባል ነበር???” በማለት፣ አመራሩ አስገዳጅ ሁኔታ ሲፈጠር ብቻ ምላሽ መስጠቱን ተችታለች።



ፍሬ ሐመር የደቡብ ኢትዮጵያ ጤና ቢሮን “በሽታው በመጀመሪያ ደረጃ የተገኘው፣ ሰው በብዛት እየሞተ ያለው… ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አሪ ዞን ጅንካ ነገር ግን ጥሩ በትኩረት እየተሰራ ያለው ሲዳማ ክልል” መሆኑን ገልጻለች።
ክልሉ “ባለሞያ ማባረር ብቻ ነው አቅሙ” ብላ በመውቀስ፣ በየሚዲያው የምናየው “ላፕቶፕ ምናምን ሲያድል ነው” ስትል፣ ትኩረት በመስክ ላይ ለሚታገለው ባለሙያ ሳይሆን “ቢሮ ውስጥ ቁጭ ብሎ ለሚሰራው” እንደሆነ ጠቁማለች።
ወጣቷ ፍሬ ሐመር ቱርሚ ዋስትና ተከልክላ ከሁለት ሳምንት በላይ በእስር ላይ ትገኛለች።
ፍሬ ሐመር ቱርሚ በፖሊስ መምሪያ ታስራ ፍርድ ቤት ሳትቀርብ መቆየቷ፣ የዜጎችን ሕገ መንግሥታዊ የመጠየቅ እና የመዳኘት መብት የሚጥስ ድርጊት ነው።
ቤተሰቦቿ ለWT Media ሲገልፁ “ዞኑ ትችትን ወንጀል የሚያደርግ ሕግ ካጸደቀ ቀድሞ ለሕዝቡ ቢያሳውቅ መልካም ነው” ያሉት የቅርብ ወገኖቿ፣ ከመሃል ብድግ ብሎ ንጹህ ሰውን አስሮ ማንገላታት “ነውር” ነው ሲሉ ወቅሰዋል።
ጉዳዩን መመልከት የሚችሉ የክልል ባለሥልጣናት ይህን ድርጊት እንዲያስቆሙ በመማፀን “ይህች እንስት ማኅበረሰብን ለመጥቀም ደፋ ቀና የምትል ሴት ናት። እንዲህ አይነት ሴትን አስሮ ማሰቃዬት በሴትነት ላይ የማመጽ አጉል ክፋት ነው” በማለት ዞኑን እንዲመለከቱት ጠይቀዋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደቡብ ዞን ዲማካ ከተማ የታሰረችውን ወጣት ፍሬ ሐመር ቱርሚን በተመለከተ፣ WT Media የሚመለከታቸውን የአሪ ዞን እና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባለሥልጣናት አግኝቶ ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።
🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏
Voice of Marginalized Community – WT Media