በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እና ኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ ላይ የሚገኘው ነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ፣ በሁለቱ ክልሎች የ’ይገባኛል’ ጥያቄ ምክንያት የሕልውና አደጋ ተጋርጦበታል።
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ፓርኩን የማስጠበቅ ኃላፊነት እንደሚወስዱ ዛሬ ቢገልጹም፣ በሁለቱ ዞኖች መካከል በተሰጠው ምላሽ ላይ መሠረታዊ ልዩነት መኖሩ ግልጽ ሆኗል።
በወቅቱ የጉጂ ዞን ኮሙኒኬሽን ኃላፊ ዳዊት ዘለቀ ለአሐዱ ሬዲዮ በሰጡት ምላሽ፣ ነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ በኦሮሚያ ከሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎች መካከል አንዱ መሆኑን አሳውቀዋል።
ወደ ፓርኩ የገቡ ሰፋሪዎች መኖራቸውን እንደማያውቁ የገለጹት ኃላፊው፣ “ነዋሪዎቹ የሚገኙትም በነባር ይዞታቸው እና በክልላቸው ነው” ብለዋል። ከአጎራባች ክልሎች በሕገ-ወጥ መንገድ ገብተዋል የሚለው መረጃ ፈጽሞ የተሳሳተ መሆኑንም አስረድተዋል።
በወቅቱ የጋሞ ዞን መንግሥት ኮሙኒኬሽን መምሪያ፣ ከኦሮሚያ ጉጂ አካባቢዎች የመጡ ከአንድ ሺሕ በላይ አባወራዎች ወደ ፓርኩ ከ25 ኪሎ ሜትር በላይ ገብተው በመስፈራቸው ምክንያት 50 በመቶ በላይ የፓርኩ ይዞታ ከታቀደለት ዓላማ ውጭ እየሆነ መሆኑን አስታውቀዋል።
ሰፋሪዎቹ በፓርኩ ውስጥ መኖሪያ ቤትና ትምህርት ቤቶችን የገነቡ ሲሆን፣ የግጦሽ እንስሳት በማሰማራት ጥብቁን ደን እያወደሙ፣ እንስሳትን እያደኑ፣ እንዲሁም ብርቅዬ እንስሳት ላይ የመጥፋት አደጋ እየጋረጡ ነው ተብሏል።
የሕገ-ወጥ ሰፋሪዎችን ለማስወጣት ከኦሮሚያ ክልል ባለድርሻ አካላት ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈርሞም ወደ ትግበራ አለመግባቱ ለችግሩ መስፋፋት ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።
አሐዱ ሬዲዮ በሁለቱ ክልሎች የ’ይገባኛል’ ጥያቄ ምክንያት አደጋ ላይ የወደቀውን የፓርኩን ሕልውና ጉዳይ ለማጣራት የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣንን ጠይቋል።
የባለሥልጣኑ ምክትል ዳይሬክተር ሰለሞን መኮንን ፓርኩ በሁለቱ ክልሎች የሚገኝ መሆኑንና ሕገ-ወጥ የደን ጭፍጨፋና አደን እየተካሄደበት እንደሆነ አምነው፣ “የሚነሳበት የባለቤትነት ጥያቄ በጥናት ያልተረጋገጠ ነው” ብለዋል።
ከምዕራብ ጉጂ ዞን ሕገ-ወጥ ሰፋሪዎች መኖራቸውን የገለጹት አቶ ሰለሞን፣ ‘ቦታው የሰፋሪዎቹ ነባር ይዞታ ነው’ የሚለው ግን የተሳሳተ መረጃ እንደሆነ አብራርተዋል።
ምክትል ዳይሬክተሩ “ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ለመሰጠት እየተሰራ ይገኛል” ሲሉ፣ ከዚህ በፊት በሁለቱም ወገን የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመፍታት የጋራ የምክክር መድረክ መዘጋጀቱን አስታውሰዋል።
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በአርባምንጭ የሰላም መድረክ ላይ የነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክን ሕልውና የማስጠበቅ ኃላፊነት እንደሚወስዱና ከሁለቱም ክልሎች አመራሮች ጋር እንደሚሠሩ መግለጻቸውን ተከትሎ፣ የክልሎች አመራሮች አፋጣኝ መፍትሔ በመስጠት የፓርኩን ጥፋት ማስቆም ይጠበቅባቸዋል።