የጋርዱላ-ጉማይዴ ግጭት የክልሉ አመራር ሴራ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ በጋርዱላ ዙሪያ በጉማይዴ አካባቢ እየተስተዋለ ባለው ግጭት ዋናው ጠንሳሽ ከፍተኛ የመንግሥት አመራር መሆኑ ተገለጸ።

ከአካባቢው ለWT Media በቪዲዮና በጽሑፍ የደረሱ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ በአመራሩ በተሠነዘረ ሴራ የጋርዱላ እና የጉማይዴ ሕዝቦች በጦርነት አለንጋ በግፍ እየተገደሉ ይገኛሉ።

ነዋሪዎች ለ WT Media እንደገለጹት፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የአቶ ጥላሁን ከበደ አማካሪ የሆኑት አቶ ብርሃኑ ኩናሎ ናቸው የተባሉት አመራር፣ ከርዕሰ መስተዳድሩ ጋር በመሆን “በሴራ ፖለቲካ የተካኑ” ናቸው በሚል አስረድተዋል።

አቶ ብርሃኑ ኩናሎ በጋርዱላ ዞን ውስጥ በሚገኙ ቀበሌዎች “አሸባሪ ጽንፈኛ ቡድን አደራጅተው” የጋርዱላ ዞን አስተዳደር ግንኙነት ካንታቦን በጥቅማጥቅም በመያዝ ለዘመናት ተከባብረው በአብሮነት የኖሩትን የጉማይዴ እና የዴራሼ ሕዝብን እያባሉ ይገኛሉ” ብሏል።

ይህ ሴራ ሰላማዊውን ሕዝብ እርስ በርስ እንዲጋጭ በማድረግ “ለሥልጣን ዕድሜያቸው ማራዘሚያ እንድሆን” ያለመ ነው ሲሉ ነዋሪዎቹ አትተዋል።

የጉማይዴ ነዋሪ የሆኑት አቶ ለማ ኩሩ በሰጡት አስተያየት፣ በጋርዱላ ዞን እና በዙሪያዋ በሚገኙት ሕዝቦች ላይ የመልካም አስተዳደር እጦት የጦርነት ስጋት አምጥቷል።

አቶ ለማ “በክልሉ አምራች ኃይል የሆኑትን የጋርዱላ ሕዝብም ሆነ የጉማይዴ ሕዝብን ለግል ጥቅማቸው በማንአለብኝነት በሥልጣን ሽፋን ሰላማዊን ሕዝብ ለማጫረስ፣ በየዓመቱ የኢትዮጵያ ዜጋ የሆኑትን በግፍ እያገዳደሉ ይገኛሉ” በማለት የሁኔታውን አስከፊነት ገልጸዋል።

በተመሳሳይ፣ በክልሉ በዜይሴ ሕዝብ ላይም ተመሳሳይ የፀጥታ ችግር ተፈጥሮ አርሶአደሮች ወደ ማሳ ገብተው ሰብል እንዳይሰበስቡ ተከልክለው፣ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየደረሰ ይገኛል።

ይህ ግጭት በሕዝቦች መካከል ከፈጠረው የሕይወትና የንብረት ጉዳት ባሻገር፣ ከፍተኛ አገራዊ ጠቀሜታ ያለው ከአርባምንጭ ወደ ኮንሶ የሚያደርሰው መንገድ እንዲዘጋ አድርጓል።

ለ WT Media የደረሰው መረጃ የፌዴራል መካላከያ ሠራዊት እና ፌዴራል ፖሊስ ወደ ቦታው ማቅናታቸውን ያመለክታል።

የፌዴራል መንግሥትም ሆነ የሚመለከተው የክልሉ መንግሥት አካላት ትኩረት በመስጠት “በሕዝብ መካከል ግጭት በሚጠነስሱ አመራርም ሆነ ግለሰቦች ላይ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ አለበት” ሲሉ በጥብቅ አሳስበዋል።

የአመራርን ሥልጣን ዕድሜ ለማራዘም ሲባል ወንድማማች ሕዝቦችን ማጋጨት፣ የክልሉን አመራር የፍትህና የመልካም አስተዳደር ጉድለት ማሳያ መሆኑን ነዋሪዎቹ ይፋ አድርገዋል።

🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏

Voice of Marginalized Community – WT Media