“የዎላይታ ልማት ማሕበር (ዎልማ) የገቢ ማመንጫ አድማሱን ወደ ማዕድንና ግንባታ ዘርፍ ሊያስፋፋ ይገባል” – ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና – የ WT Media ተጋባዥ ጸሐፊ
በዎላይታ ታሪክ ውስጥ ብረትን የማምረት፣ የማቅለጥ እንዲሁም ባሕላዊ የእርሻና የጦር መሣሪያዎችን የማዘጋጀት ጥበብ እጅግ አስደናቂ እንደነበረ የተለያዩ የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ።
ሆኖም ግን፣ የተለያዩ የኢትዮጵያ አገዛዞች ልማት ወዳዱን “የዎላይታ ሕዝብ ሀብታም ከሆነ የመገንጠል ጥያቄ ያነሳል” በሚል ዘመኑን ያልዋጀ የተሳሳተ እሳቤ በመመራት፣ በአካባቢው ላሉ ተፈጥሮአዊ ሀብቶች ትኩረት ሳይሰጡ ቆይተዋል።
በአሁኑ ሰዓትም ቢሆን በዎላይታ የሚገኙ ማዕድናትን ደረጃውን በጠበቀ ጥናት ለይቶ ማወቅ ተችሏል ማለት አይቻልም። ይህም የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ርብርብ የሚጠይቅ ጉዳይ ነው።
በአሁኑ ወቅት በዎላይታ ከፍተኛ መጠን ያለው የድንጋይ ከሰል ክምችት እንደሚገኝና የተወሰኑ ባለሀብቶችም በዘርፉ መሰማራታቸው ይታወቃል። ይሁን እንጂ እነዚህ ባለሀብቶች በሂደት በክልሉ የተለያዩ እንቅፋቶች እንደደረሱባቸው የአደባባይ ምስጢር ነው።
ለግል ባለሀብቶች ምቹ ሁኔታን መፍጠር ጠቃሚነቱ አይተኬ በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡት እያሳሰብኩ፣ ወደ ዋናው ነጥቤ ልመለስ።

የዎላይታ ልማት ማሕበር (ዎልማ) የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ለመሥራት የገቢ ማስገኛ ተግባራት ላይ መሰማራቱ ይታወቃል። ዛሬ ማንሳት የምፈልገው ጥያቄ ግን “ዎልማ ለምን በዞኑ የድንጋይ ከሰል ማውጣት ሥራ ላይ አይሰማራም?” የሚል ነው። ድርጅቱ በዘርፉ መሰማራት ያለበትባቸው ምክንያቶችና የመፍትሔ ሐሳቦች እንደሚከተለው ቀርበዋል፦
የካፒታል ችግርን መቅረፍ፦
የካፒታል እጥረት ካለ የዞኑ መንግሥት የተለያዩ ድጋፎችንና የግብር እፎይታዎችን ሊሰጥ ይገባል። ሥራውን በአነስተኛ መጠን መጀመር የሚቻል ሲሆን፣ ካልሆነም ለዚሁ ዓላማ ገቢ ማሰባሰብ ወይም አብዛኛውን ድርሻ ዎልማ ይዞ ቀሪውን ለሕዝቡ በአክሲዮን መልክ መሸጥ ይቻላል።
ከፍተኛ የገንዘብ እንቅስቃሴ፦
በዘርፉ የተሰማሩ መጠነኛ አቅም ያላቸው ባለሀብቶች እንኳን የሚያንቀሳቅሱት ገንዘብ በቢሊዮኖች የሚቆጠር በመሆኑ፣ ዎልማ ይህንን ዘርፍ ሊንቀው አይገባም።
ለልማት ሥራዎች የሚኖረው ፋይዳ፦
ከዚህ ዘርፍ በሚገኝ ገቢ ዎልማ የተሻለ የገንዘብ ነጻነት አግኝቶ ትልልቅ ሥራዎችን መሥራት ይችላል። ለምሳሌ፦ አስፋልት መንገዶችንና ድልድዮችን መገንባት፣ እንዲሁም ይገነባል ለተባለው ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላል።
ወደ ኢንዱስትሪ መሸጋገር፦
ዎልማ ጠንክሮ ከሠራ የመጀመሪያ ደረጃ (Primary sector) ከሆነው ማዕድን ማውጣት ወደ ሁለተኛ ደረጃ (Secondary sector) በመሸጋገር እሴት የመጨመር (Value add) ሥራዎችን ሊሠራ ይችላል።
የሕዝብን ሀብት ለሕዝብ በተሻለ መልኩ ማዋል ከተፈለገ፣ የዎላይታ ልማት ማሕበር በዚህ የማዕድን ዘርፍ ላይ መሰማራቱ ለዞኑ ሁለንተናዊ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አያጠራጥርም።
በፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና – የ WT Media ተጋባዥ ጸሐፊ የቀረበ ነው
🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏
Voice of Marginalized Community – WT Media