GridArt_20260502_180617969

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በጎፋ ዞን ባለፈው አመት ለደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ ተጎጂዎች የተሰበሰበ ወደ አንድ ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ የት እንደገባ ባልታወቀበትና በቼክ ማጭበርበር የተጠረጠሩ ግለሰቦች ጉዳይ ገና እልባት ባላገኘበት ወቅት፣ በገዜ ጎፋ ወረዳ አንድ አምቡላንስ ለሽያጭ መቅረቡ ከፍተኛ ቅሬታ መቀስቀሱ ተገልጿል።

የገዜ ጎፋ ወረዳ ነዋሪዎች ለአምቡላንስ ሽያጭ የወጣውን የጨረታ ማስታወቂያ በመቃወም ለ WT Media ቅሬታቸውን አቅርበዋል።

ነዋሪዎቹ እንደሚሉት፣ በወረዳው የሚታየው ከፍተኛ የአምቡላንስ እጥረትና የሪፈራል ሥርዓት መዛባት የዜጎችን ሕይወት ለከፋ አደጋ እያጋለጠ ነው።

ነዋሪዎቹ ከወር በፊት በውዘቴ በደረሰ የመኪና አደጋ የቆሰለች ወጣት፣ ወደ ዎላይታ ሶዶ ሆስፒታል ለመሄድ አምቡላንስ በማጣቷ ሕይወቷ ማለፉን እንደ አብነት ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅት ያለችው ጥቂት አምቡላንስ ወደ ጃውላ፣ በድሮ ወይም ውዘቴ ቀበሌዎች ከሄደች፣ ሌላው ታካሚ እስኪመለስ ጠብቅ በሚባልበት አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ይገኛል።

ያለውን አምቡላንስ ጠግኖ ወደ ሥራ ከመመለስ ይልቅ ለሽያጭ ማውጣት “በሰው ሕይወት ላይ እንደመቆመር ይቆጠራል” ብለዋል።

ማህበረሰቡ ለገዜ ጎፋ ወረዳ አስተዳደር እና ለዞኑ ጤና መምሪያ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ሰንዝሯል፦

  1. አምቡላንሱን ለመሸጥ የተገደደበት ተጨባጭ ምክንያት ምንድን ነው?
  2. ለሽያጭ የቀረበው አምቡላንስ የተሻለ ምትክ ዕቅድ ተዘጋጅቶለታል?
  3. የአካባቢው ልማት የሚለካው በዜጎች ደኅንነት ነው ወይስ በንብረት ሽያጭ?

በጉዳዩ ዙሪያ WT Media የሚመለከታቸውን የወረዳውና የዞኑን የሥራ ኃላፊዎች ለማነጋገር ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም፣ ኃላፊዎቹ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ሳይሳካ ቀርቷል።

ባለፈው አመት በዚህ ዞን ለደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ ተጎጂዎች የተሰበሰበ ወደ አንድ ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ የት እንደገባ ባልታወቀበትና በአደጋ ተጎጂዎች ስም የተሰበሰበ 60 ሚሊዮን ብር በቼክ ሊመዘበር ሲል እጅ ከፍንጅ ተይዞ ጉዳዩ በዝምታ በታለፈበት በዚህ ወቅት፣ መሰል የንብረት ሽያጭ ውሳኔዎች በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ያለውን አለመተማመን ይበልጥ ያሰፋዋል።

በመሆኑም የወረዳው መንግሥት ሂደቱን በአስቸኳይ እንዲያቆም እና ለሕዝቡ ግልጽ ማብራሪያ እንዲሰጥ እንጠይቃለን።

🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏

Voice of Marginalized Community – WT Media