በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዎላይታ ዞን፤ ዳሞት ወይዴ ወረዳ አንካ ሻሻራ ቀበሌ ለ12 ዓመታት ያህል 81.2 ሄክታር የሕዝብ ወል መሬት በሕገወጥ መንገድ ተወሮ መቆየቱ እና አሁን ላይ የተጀመረው የዕርምት እርምጃ በብዙዎች ዘንድ አድናቆትን ቢያገኝም፤ በሌላ በኩል ግን በሕዝቡና በታዛቢዎች ዘንድ እጅግ አንገብጋቢ የሆኑ የፍትሕና የተጠያቂነት ጥያቄዎችን አስነስቷል።
ሕዝቡ በምሬት እየጠየቀ ያለው ዋነኛ ጥያቄ፦ “ይህ ግዙፍ የመሬት ወረራ ሲካሄድ ለ12 ዓመታት ሙሉ በአካባቢው የወረዳና የዞን አመራር አልነበረም ወይ? የወረዳው የመሬት አስተዳደር ቢሮ፣ የፍትሕ አካላት እና የጸጥታ መዋቅሩ የት ነበሩ?” የሚል ነው።
WT Media ከጉዳዩ በስተጀርባ ያለውን መዋቅራዊ የአመራር ጉድለት፣ ሌብነት፣ መጭበርበር እና የፍትሕ መጓደል በሚከተሉት ነጥቦች ይተነትናል።
WT Media ከታማኝ ምንጮች ባገኘው ጥልቅ መረጃ መሠረት፤ ይህ ወንጀል መሬት በመንጠቅ ላይ ብቻ ያበቃ ሳይሆን ማኅበር ለሚያደራጁ ምስኪን ወጣቶች ተብሎ የተመደበውን በመቶ ሚሊዮን ብር የሚቆጠር ተዘዋዋሪ ፈንድ (የብድር ገንዘብ) ጭምር በአካባቢው ባለሥልጣናት ኔትወርክ የተመዘበረበት ታላቅ ታሪካዊ ክህደት ነው።
ከ200 ሺህ በላይ የተማሩ የሥራ አጥ ወጣቶች ባሉበት በዎላይታ ዞን ይህ ዓይነቱ ስልታዊ በደል በአንድ ወረዳ ብቻ ሳይሆን በመላው የዞኑ ወረዳዎች ውስጥ እያረገፈ ያለው ጠባሳ በአስቸኳይ ሊፈተሽና ሊመረመር ይገባል።
በዳሞት ወይዴም ሆነ በሌሎች የዎላይታ ወረዳዎች ወጣቶች በከብት ዕርባታ፣ በግብርና እና በተለያዩ ዘርፎች በማኅበር ሲደራጁ የመንግሥት መዋቅር መሬት ብቻ ሳይሆን የሥራ ማስጀመሪያ የሚሆን በመቶ ሚሊዮን ብር የሚቆጠር ተዘዋዋሪ ፈንድ (የብድር ገንዘብ) መድቦ ነበር።
ነገር ግን የWT Media እንዳረጋገጠው፤ ለአብነትም መሬቱን እንደ ቀበሌው ሥራ አስኪያጅ እና እንደ አቶ ማቱሳል ቲቶ ያሉ ጥቅመኞች ሥልጣንን መከታ በማድረግ ለ12 ዓመታት ለግል ዓላማቸው ሲጠቀሙበት ለወጣቶቹ ተብሎ የመጣው በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር የብድር ገንዘብም በተመሳሳይ መልኩ “ለወጣቶች ተሰጥቷል” በሚል የሐሰት ሪፖርት በየደረጃው ባሉ ከፍተኛ የወረዳና የዞን አመራሮች ኪስ ውስጥ ገብቷል።


ወጣቶቹ መሬቱንም ሆነ የተመደበላቸውን የገንዘብ ብድር ሳያዩ ባለሥልጣናትና ዘመዶቻቸው ግን በወጣቶች ስም በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር የሕዝብ ሀብት አካብተውበታል።
በአሁኑ ወቅት በዎላይታ ዞን ውስጥ ከ200 ሺህ በላይ የተማሩ፣ ዲግሪና ዲፕሎማ ይዘው የሥራ ዕድል ያጡ ወጣቶች ይገኛሉ። እነዚህ ወጣቶች በገዛ ሀገራቸውና በትውልድ ቀያቸው ሰርተው ለመለወጥ በማኅበር ሲደራጁ፣ ዕድላቸው በጥቂት ስግብግብ ባለሥልጣናት ይጨናገፋል።
ይህንን ተከትሎ የሚመጣው ማኅበራዊ ቀውስ እጅግ የከፋ ነው። ለሥራ ዕድል ፈጠራ የተመደበላቸውን መሬትና ብድር የተነጠቁ ወጣቶች ተስፋ በመቁረጥ ለከፋ ስደት ይዳረጋሉ።
በአንካ ሻሻራ ቀበሌ እንደታየው የማኅበሩ አባላት የነበሩ ወጣቶች ተበታትነው የተወሰኑት ሴት አባላት ወደ አረብ ሀገር የተሰደዱት በዚህ መዋቅራዊ ዝርፊያ ምክንያት ነው።
ይህ የአንድ ወረዳ እውነት ሳይሆን በመላው የዎላይታ ዞን ወረዳዎች ያለ አጠቃላይ ሀቅ ነው። በየወረዳው የተማሩ ወጣቶች ስም እየተነገደበት በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ብድር ለባለሥልጣናት ዘመዶች ይከፋፈላል፤ እውነተኛው የደሃ ልጅ ግን የሥራ አጥነቱን ቁጥር እያደመቀ በባዶ እግሩ ይሄዳል።
ይህ ግዙፍ መሬት ሲወረርና በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ፈንድ ሲመዘበር ላለፉት 12 ዓመታት ሙሉ (ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ) የወረዳና የዞን አመራሮች “አላወቅንም” ሊሉ ፍጹም አይችሉም። ወረራውና የምዝበራ ሰንሰለቱ የተካሄደው የመንግሥትን ሥልጣን መከታ በማድረግ እንደመሆኑ መጠን የታችኛው የቀበሌ ሥራ አስኪያጅ ብቻ ሳይሆን በየዘመናቱ የተፈራረቁ የየወረዳው ከፍተኛ አመራሮች፣ የመሬትና የፋይናንስ ኃላፊዎች የጥቅሙ ዋና ተባባሪዎች ናቸው።
አሁን የቀበሌውን ሥራ አስኪያጅ በቁጥጥር ሥር በማዋል ብቻ “ተጠያቂነት ሰፈነ” ማለት አይቻልም። እውነተኛ ፍትሕ ሊመጣ የሚችለው፣ ላለፉት 12 ዓመታት በየደረጃው የነበሩና የወጣቱን ተስፋ የበሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ተለይተው ለሕግ ሲቀርቡና የተመዘበረው በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር የወጣቶች ፈንድ ተለይቶ ሲመረመር ብቻ ነው።
እንደ አስተያየት ሰጪዎች ገለፃ በዎላይታ ዞን የተማሩ ወጣቶች ቁጥር ከ200 ሺህ በላይ በሆነበት በአሁኑ ወቅት የወጣቶችን ተስፋና ለነሱ የተመደበውን መሬትና በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር የብድር ፈንድ መስረቅ በሕዝብ ላይ የተፈጸመ ታላቅ ክህደት ነው። ይህ አደገኛ ዝንባሌ በአስቸኳይ በጥልቀት ሊፈተሽና ሊመረመር ይገባል!
ይህንን በመላው ዞኑ ወረዳዎች የተንሰራፋውን የወጣቶች መሬትና የብድር ፈንድ ምዝበራ ጉዳይ በሁሉም ቦታ ምርመራ ተካሂዶ፤ የታችኞቹን ትናንሽ ዓሦች ብቻ ሳይሆን ላለፉት 12 ዓመታት የወጣቱን ዕድል የበሉትን “ትላልቅ ዓሦች” (ከፍተኛ አመራሮችን) ለሕግ እንዲቀርቡ በጥብቅ እናሳስባለን ሲሉም ገልጸዋል።