GridArt_20260803_164422881

​ዎላይታ ሶዶ ባለሰባት በር ናት ስንል ለማውራት ብቻ አይደለም። ዎላይታ ለብዙ አዋሳኝ ዞኖች እንዲሁም ለማዕከላዊ መንግስት መቀመጫ ቅርብና ማዕከል ናት ስንል የዎላይታ ካድሬ ተሰባስቦ የወሰኑትና የሰጡት ሳይሆን ፈጣሪ የቸራት የደቡቧ ሆርሙዝ ናት።

​በዚህ አካባቢ የሚሰራው የልማት ሥራ ለዎላይታ ብቻ ሳይሆን ለመላው ጎረቤት ህዝብ ጭምር ነው። የወላይታ ልማት ሲዳከም የጎረቤት ዞኖች ልማት ይዳከማል።

ለምሳሌ፦ ​የዎላይታ-ጂንካ መንገድ መስተጓጎል ታታሪው የጎፋ፣ የአሪና ባስኬቶ እንዲሁም የቁጫ ህዝብ የሚያመርተው ሰሊጥ፣ ቡናና ቅመማ ቅመም ዝውውር ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራል።

​ወደ ግቤ 3 ያለው መንገድ ሲስተጓጎል የዳውሮና ኮንታ ህዝብ የሚያመርተው ብራንድ ቅቤና ማር እንዲሁም ፍራፍሬ ምርቶች ይጎዳሉ።

​ከዎላይታ-ደቡብ ኦሞ መንገድ ልማት ሲስተጓጎል የኮንሶ፣ ኮሬ፣ ጋርዱላና ቡርጂ ማኛ ጤፍና ቡላ እንዲሁም ከደቡብ ኦሞ፣ ኮንሶና አሌ ኤክስፖርት የሚደረገው የፍየልና የበግ ሙክቶች፣ የጥጥ ምርት እና የጨንቻ አፕል ዝውውር ይስተጓጎላል።

​ከዚህ በተጨማሪ ዎላይታ ለሀላባ በርበሬ፣ ለካምባታና ጣንባሮ ቡናና ቆጮ፣ ለሀዲያው ስንዴና ጤፍ ምርት ትልቅ ገበያ ማዕከል ሆና የምታገለግል ትክክለኛ የደቡቧ ሆርሙዝ ናት ስንል ለዚህ ሁሉ ማዕከልና መተላለፊያ እንዲሁም የገበያ ዕድል በመሆኗ በዎላይታ ምድር የሌለ ነገር የምንለው በምክንያት ነው።
​
​ከዚህ ባሻገር ዎላይታ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን በከፍተኛ ሁኔታ በማምረት ለውጭ ገበያ ጭምር ኤክስፖርት የምታደርገው ቀይ የዎላይታ ቦሎቄ፣ ቡናና ቅመማ ቅመም፤ ለዘይት ምርት የሚሆን የጋሌ፣ የወይዴ፣ የስሶሬና የሆቢቻ አቮካዶ፣ እንዲሁም በሁሉም ወረዳዎች በስፋት እየተመረተ ገበያን ያረጋጋው ጣፋጭ ሙዝ፣ ማንጎ እና ፓፓያ በከፍተኛ ሁኔታ ይመረቱባታል።

​ከእንስሳትና ዓሳ ሀብት አኳያ ከዋዱ ጊዜ ጀምሮ በተሰራው ሥራ ከፍተኛ የሆኑ ዝርያቸው የተሻሻሉ ከ38 ሊትር በላይ ወተት የሚሰጡ ላሞች አሉ። በዎላይታ ሶዶ ከተማ ብቻ በአንድ ቤት ውስጥ ከ20 በላይ የወተት ላሞች በመኖራቸው የወተት ምርት በስፋት የሚመረት ሲሆን፣ የቁርጥ ሳንጋዎችን ማየት ይቻላል።

​የአባላና ሁምቦ እንዲሁም የኦፋና ኮይሻ የፍየል ቱማሌሳዎች፣ የዶሮ ስርጭትና ምርት ሲታይ፣ በቀድሞው ክልልም ሆነ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የዶሮ ስርጭት ይገኛል። የዋዱ ዶሮ እርባታ ማዕከል ያለበት በመሆኑ ለየት ያሉ «የዎላይታ ዶሮዎች» ተብሎ በልዩነት የሚታወቁ ጣፋጭ ሥጋ ያላቸው ዶሮዎችና የዶሮ ምርቶች ይገኙበታል።

ከዓሳ ሀብት አንጻር ትልቁ ኦሞ ወንዝ በግቤ 3 ግድብ ምክንያት ሐይቅ በመሆኑ ከ120 ኪሎ ግራም በላይ የሚመዝኑ የናይል ፓርች (አባያ ሐይቅ የሚወጣ ልዩ ጣዕም ያለው)፣ እንዲሁም ብላቴ፣ ሐመሳ እና ሌሎች የውሃ አካላት ሀብቶች በስፋት ይገኛሉ።
​
​በአጠቃላይ ዎላይታ ሶዶ ለቀጠናው ያላት ጂኦፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቁመና ከማዕከልነት የዘለለ ለጎረቤት ዞኖች ሁሉ ሕልውና እና ዕድገት ወሳኝ የደም ዝውውር ናት። የአካባቢው የንግድ፣ የትራንስፖርት፣ የግብርና እና የኢንዱስትሪ አቅም ማዕከል መሆኗ የደቡቧ «ሆርሙዝ» የሚያሰኛትን ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ ጸጋ በጉልህ ያሳያል።

ስለዚህ የዚህችን ከተማ እና አካባቢ ሰላም፣ ልማት እና መሠረተ ልማት መጠበቅና መጠየቅ ለመላው አዋሳኝ ህዝቦች የጋራ ህልውና ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው።