GridArt_20261018_143113157

​የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጸሙትን ጥቃቶች ከተገንጣይ ቡድኖች እንቅስቃሴ እና ከሽብር ተግባራት ጋር አያይዘው ገልጿል።

ሚኒስትሩ ላለፉት ጥቂት ሳምንታት ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር እየተዋጉ የሚገኙትን ኃይሎች “ተገንጣይ ቡድን” ሲሉ ጠርተውታል።

​ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በንግግራቸው የኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባን ዒላማ ያደረገ የድሮን ጥቃት መፈጸሙን በመጠቆም ድርጊቱን አውግዘዋል።

“ማንም ቢሆን ሽብርተኝነትን፣ በዋና ከተማቸው ላይ የተፈጸመውን የድሮን ጥቃቶች ጨምሮ የሚደግፍ የለም” ሲሉም ገልጸዋል።

አሜሪካ የኢትዮጵያ መንግሥት ከእነዚህ ተገንጣይና የሽብር ተግባር ከሚፈጽሙ ኃይሎች የሚሰነዘርበትን ፈተና በሚገባ እንደምትረዳም አረጋግጠዋል።

በተገንጣይ ቡድኖች እንቅስቃሴ እና በተወሰዱት ምላሾች ምክንያት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ድንበሮች አቅራቢያ የጦር ኃይሎች ክምችት መጨመሩን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ሁለቱም ሀገራት ወታደሮቻቸውን ወደ ድንበር ማስጠጋታቸው ሌሎች ጎረቤት ሀገራትን ጭምር የሚያካትት ሰፊ ቀጠናዊ ጦርነት ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው አመልክተዋል።

“ዓለም በአሁኑ ሰዓት ሌላ ተጨማሪ ጦርነት አይፈልግም” ብለዋል።

​በቅርቡ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር በተያያዘ ጥላቸው የነበረውን አነስተኛ የጦር መሣሪያ ማዕቀብ ያነሳችው ከሁለቱም ወገኖች ጋር በመነጋገር የሰላም አስከባሪነት እና የአደራዳሪነት ሚናዋን ለመወጣት እንደሆነና ይህም ከወቅታዊው ሁኔታ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንደሌለው አስረድተዋል።

አሜሪካ ከኤርትራ ጋር ላለፉት ዓመታት የጠበቀ ግንኙነት ያልነበራት ቢሆንም ባለፉት ጥቂት ወራት ከተለመደው የተሻለ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ መቻሏን ገልጸው፤ በአንጻሩ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር እጅግ የጠበቀና ጠንካራ ግንኙነት እንዳላት አጽንኦት ሰጥተዋል።
​
ሩቢዮ በዚህ ሳምንት ከኢትዮጵያ ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ጠቁመው፣ ሀገራቸው ኢትዮጵያ ከሚገጥማት ፈተና አንጻር አቋሟን እንደምትረዳ ቢገልጹም፤ መንግሥት ለተገንጣይ ቡድኖች የሚሰጠው ምላሽ ጥበብ የተሞላበትና ሚዛናዊ ሊሆን እንደሚገባው አሳስበዋል።

እርምጃው ሌሎች ሀገራትን አሳትፎ ወደ አውዳሚ እና የሰፋ ጦርነት እንዳያመራ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።