በሞያሌ ከተማ በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች ወሰን አካባቢዎች የግጭት ውጥረት ነግሷል፤ የአካባቢው ነዋሪዎች ስጋት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን እና በሶማሌ ክልል አዋሳኝ በሆነችው ሞያሌ ከተማ ከትናንት ጀምሮ በተቀሰቀሰ አዲስ ግጭት ምክንያት በከተማዋ ከፍተኛ የጸጥታ ውጥረት መንገሱንና የከባድ መሳሪያ ተኩስ ድምፅ እየተሰማ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ለWT Media ገልጸዋል።

እንደ ነዋሪዎቹ ገለፃ ከሆነ፤ የግጭቱ መነሻ በኦሮሚያ ክልል አወሳኝ ድንበር በኩል የሚገኝን ቤት የገዙ አንድ የሶማሌ ተወላጅ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልልን ባንዲራ በቦታው ላይ መስቀላቸውን ተከትሎ በተፈጠረ አለመግባባት ነው። “በእኛ አስተዳደር ድንበር ላይ የሌላ ክልል ባንዲራ እንዴት ይሰቀላል?” በሚል በተነሳ የቃላት ክርክርና እሰጥ-አገባ፣ ሁኔታው በፍጥነት ወደ ተኩስ ልውውጥ መሸጋገሩ ተነግሯል።
በተከፈተው ተኩስም በኦሮሚያ ክልል በኩል አንዲት ህጻን ህይወቷ ማለፉ የተገለፀ ሲሆን፤ ከዚህ በኋላ ሁኔታው ይበልጥ ተፋፍሞ ወደ ሰፊ ግጭት ማደጉን ምንጮቻችን አረጋግጠዋል።
WT Media ዛሬ ከቀኑ 6:00 በሞያሌ ከተማ ውስጥ ተሸሽገው የሚገኙ ነዋሪዎችን በስልክ ባናገረበት ወቅት ከበስተጀርባ የከባድ መሳሪያና የጦር መሳሪያዎች ተኩስ ድምፅ በጎልህ ይሰማ ነበር።
እንደ ምንጮቻችን ገለፃ አካባቢው ላይ የነበሩ የመከላከያና የፌደራል ሰራዊት አባላት ሁኔታውን ለመቆጣጠር ባደረጉት ጥረት ለውጥ ባለመመጣቱ ከስፍራው መውጣታቸውን ተከትሎ በአሁኑ ወቅት የሁለቱ ክልሎች የፖሊስ ኃይሎች በከተማዋ ውስጥ ተኩስ ልውውጥ እያደረጉ ይገኛሉ።
ዛሬ ከጠዋት ጀምሮ እስከ ቀትል 6፡00 ሰዓት (በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር) ድረስ ያልተቋረጠ የተኩስ ድምፅ እየተሰማ ይገኛል።
በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች ህይወታቸውን ለማዳን ወደ ጎረቤት ኬንያ (ጋምቦ አካባቢ) እና ወደ ሌሎች ደህና ቦታዎች በመሸሽ ላይ ናቸው።
በከተማዋ በንግድ ስራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች (በተለይም ከደቡብ ክልል ከዎላይታ፣ ሀድያ እና ሌሎች አካባቢዎች) የመጡ ዜጎች ስራቸውን አቁመው በከፍተኛ ስጋት ውስጥ ይገኛሉ።
በአሁኑ ወቅት በሞያሌ ከተማ እና አካባቢዋ አጠቃላይ የትራንስፖርት አገልግሎት፣ የንግድ እንቅስቃሴ እና የህዝብ ተንቀሳቃሽነት ሙሉ በሙሉ ተስተጓጉሏል። በጥቅሉ በሰው ህይወትና አካል ላይ የደረሰው ጉዳት መጠን እስካሁን በውል ያልታወቀ ቢሆንም በርካታ ሰዎች መቁሰላቸውና ከፍተኛ የንብረት ውድመት ስጋት መኖሩ ተገልጿል።
የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት ከሆነ፤ የሚመለከተው የፌደራል መንግሥትና የጸጥታ አካላት በአስቸኳይ ጣልቃ ገብተው ግጭቱን ካላቆሙት ሁኔታው ወደ አስከፊና ሰፊ ቀውስ ሊያመራ ስለሚችል አጣዳፊ የመፍትሔ እርምጃ እንዲወሰድ ተማጽነዋል።