የኦቶና ሆስፒታል ቀውስ ወደየት? ታካሚዎች ከህዝብ ሆስፒታል ወደ ባለሙያዎች የግል ክሊኒክ ለምን ይነገዳሉ?
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኘው የዎላይታ እና አጎራባች ህዝብ መሠረታዊ የህክምና መብቶች እና የጤና አገልግሎት ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ከጊዜ ወደ ጊዜ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።
WT Media ከኦቶና ሆስፒታል የህክምና ባለሙያዎች፣ ከተጎጂ ታካሚዎች እና ከቀድሞ መረጃዎቻችን ጋር በማቀናጀት ባጠናቀረው አጠቃላይ ዳሰሳ መሠረት ተቋሙ ለከፍተኛ ውድቀት፣ ለግብዓት እጥረት እና ለውስጣዊ ፀረ-ህዝብ ተግባራት መጋለጡን አረጋግጧል።
ለአንድ መቶ ዓመታት ያህል ለዎላይታ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን አጎራባች አካባቢዎችን ጨምሮ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ነፍስ ሲታደግ የቆየው ታሪካዊው የኦቶና ሆስፒታል ምክንያቱ ባልታወቀ የእሳት አደጋ ከወደመበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ተገቢው ምላሽ ባለማግኘቱ አሳሳቢ ሰብአዊ ቀውስ እየፈጠረ መሆኑ ይታወሳል።

«WT Media» ከዚህ ቀደም ባደረጋቸው የምርመራ ዘገባዎች እንደገለጸው፤ ሆስፒታሉ በመውደሙ ምክንያት በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው እና በሕዝባዊ የጤና መድህን አገልግሎት ያገኙ የነበሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮችና አቅመ-ደካሞች ብቸኛ አማራጫቸውን አጥተው ለከፍተኛ መከራ ተጋልጠዋል።
«ኦቶና ሆስፒታል ታመመ፤ እናክመው!» በሚል መሪ ቃል የደቡብ ክልል ፕሬዝዳንት የነበሩት አቶ ጥላሁን ከበደ ለሆስፒታሉ መልሶ ግንባታ ጥሪ ካስተላለፉ ቆይታዎች ቢቆጠሩም እስካሁን ድረስ ግንባታው አለመጠናቀቁ እና ለሆስፒታሉ ተብሎ የተሰበሰበው ገንዘብና ቁሳቁስ የገባበት ባለመታወቁ በህብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታን ቀስቅሷል።
በወቅቱ የክልሉ እና የዞኑ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ለጉዳዩ የሰጡት ትኩረት አነስተኛ መሆን እና የሪፈራል ሥርዓቱ ሙሉ በሙሉ መናጋት በየቤቱ እና በየቀበሌው የሚገኙ ዜጎች ህይወት እንዲቀጠፍ ምክንያት ሆኗል። የዘርፉ ባለሙያዎችን በማሳተፍ በተደረጉ ልዩ ዳሰሳዎች መሰረት፣ ሆስፒታሉ አገልግሎት ማቋረጡን ተከትሎ ህክምና አግኝተው መዳን የሚችሉ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ለህልውና አደጋ መዳረጋቸው ተመላክቷል።
ከኦቶና ሆስፒታል እና ከሌሎች የዞኑ ጤና ተቋማት የተሰባሰበው መረጃ እንደሚያሳየው፤ እንደ ኤምአርአይ (MRI)፣ ሲቲ ስካን (CT Scan) እና ሌሎች መሰረታዊ የህክምና ምርመራዎች በዎላይታ ዞን አለማግኘት ለህብረተሰቡ ከፍተኛ የኢኮኖሚ፣ የሞራል እና የሰዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት እየሆነ ነው።
ታካሚዎች ለእነዚህ ምርመራዎች ሲሉ ወደ ሃዋሳ እና አርባ ምንጭ ሆስፒታሎች እንዲሄዱ በመገደዳቸው ተጨማሪ የገንዘብ፣ የአካል እና የስነ-ልቦና ጫና ውስጥ ይወድቃሉ።
አርባ ምንጭ ሀዋሳ በመሳሰሉ አጎራባች ከተሞች እጅ ያሉ የመንግስት ጤና ተቋማት የላቁ የምርመራ ማዕከላት ሲኖራቸው በዎላይታ ዞን ግን ህብረተሰቡ ለዚህ እንግልት መዳረጉ የሀብት ክፍፍል እና የፍትህ እጦት ጥያቄን አስነስቷል።
የዞኑ ጤና መምሪያ፣ የክልል ባለስልጣናት እና ባለድርሻ አካላት የማይሰራ መሳሪያን በአፋጣኝ በመጠገን፣ የህዝብና የግል አጋርነትን (Public-Private Partnership) በማጠናከር እና avoidable referrals (ያለ አግባብ የሚደረጉ ሪፈራሎችን) መቀነስ እንዳለባቸው ባለሙያዎች በጥብቅ አሳስበዋል።
ባለፈው ዓመት ባልታወቀ ምክንያት በእሳት ወድሞ የነበረው የኦቶና ሆስፒታል በሁለት ወራት ውስጥ ተገንብቶ ማለቅ አለበት በሚል በአዲሱ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ተስፋዬ በልጅጌ ክትትል እየተገነባ መሆኑ ይታወሳል።
ይሁን እንጂ ሆስፒታሉ አገልግሎቱ በመቆሙ ምክንያት አነስተኛ ገቢ ያላቸው እና የጤና መድህን ተጠቃሚዎች ሕክምና ማግኘት ባለመቻላቸው ከፍተኛ ሞት እና ስቃይ እየደረሰባቸው መሆኑን WT Media በተደጋጋሚ መዘገቡ የሚታወስ ነው።
ከግንባታ መዘግየት እና ከመሳሪያ እጥረት ባሻገር በሆስፒታሉ ውስጥ የሚታየው ሌላው አስደንጋጭ ችግር ሆን ተብሎ የሚፈጸም የጥቅም ግጭት (Conflict of Interest) ነው።
አነስተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች በዋናነት የሚጠቀሙበት ኦቶና ሆስፒታል ውስጥ የሚሰሩ እና የግል ጤና ተቋማት ያሏቸው አንዳንድ ግለሰቦች ለሙያ ግዴታቸው ቅድሚያ ከመስጠት ይልቅ ለገንዘብ ማትረፍ እያደሉ ይገኛሉ።
በሆስፒታሉ ውስጥ የሚገኙ የህክምና መሳሪያዎች ሆን ተብሎ እንዲበላሹ በማድረግ ወይም አገልግሎት እንዳሰጡ በማድረግ ታካሚዎችን ወደራሳቸው የግል ክሊኒኮች በሪፈራል (Refers) ስም እየላኩ መሆኑ ተረጋግጧል።
የሆስፒታሉ ፋርማሲ ባዶ እንዲሆን በማድረግ ታካሚዎች ውድ ውጪ አውጥተው ከውጭ የግል ፋርማሲዎች እንዲገዙ የሚደረገው ግፊት ሆስፒታሉ ከግል ክሊኒኮች በታች እንዲሆን አድርጎታል የሚል ጠንካራ ውንጀላ ቀርቧል።
“ህዝብ የትም ይኑር የት ጥራት ያለው፣ ፍትሃዊ እና ተደራሽ የሆነ የጤና አገልግሎት የማግኘት መብት አለው። የኦቶና ሆስፒታል ዳግም ግንባታ በፍጥነት ተጠናቆ አገልግሎት እንዲጀምር ከመደረጉ ባለፈ በሆስፒታሉ ስም እየነገዱ እና የህዝብን ህይወት ለንግድ ዓላማ እያዋሉ ያሉ አካላት ላይ አስቸኳይ ቁጥጥርና ህጋዊ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል” በሚለው በርካቶች ይስማሙበታል።
#OtonaHospital #WTMedia #Ethiopia