Google map

“የግጭቱ ዋና ተዋናዮች አሸባሪው ህወሓት፣ ሸኔና ተባባሪዎቹ ናቸው”-ኮሎኔል አበበ ገረሱ

በምስራቅ ወለጋ ዞን ኪራሙ ወረዳ ታጣቂዎች በንፁሃን ዜጎች ላይ ባደረሱት ጥቃት የህይወትና የንብረት ጉዳት መድረሱን የጉዳቱ ሰለባ ነዋሪዎች ተናገሩ።

የግጭቱ ዋና ተዋናዮች አሸባሪዉ ህወሓት፣ ሸኔና ተባባሪዎቹ ናቸው ሲሉ የኦሮሚያ ክልል አስተዳደርና ጸጥታ ቢሮ አማካሪ ኮሎኔል አበበ ገረሱ ገልጸዋል።

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን የኪራሙ ወረዳ ነዋሪዎች እንደተናገሩት፤ ከመስከረም 30/2014 ዓ.ም ጀምሮ በአካባቢው ልዩ ስሙ ሃሮ በሚባል ስፍራ ታጣቂዎች በንፁሃን ላይ በከፈቱት ተኩስ ሰዎች ተገድለዋል፣ ንብረታቸው ተዘርፏዋል፣ ከቀዬያቸው ተፈናቅለዋል። በጥቃቱ ከተገደሉ ንፁኃን በተጨማሪ የገቡበት ያልታወቀ ዜጎች መኖራቸውን አረጋግጠዋል።

እንደ ነዋሪዎቹ ገለፃ፤ በጥቃቱ ከሰዎች ህልፈትና መፈናቀል ባለፈ ሀብትና ንብረት ወድሟል፣ ዝርፊያ ተፈፅሟል እንዲሁም ተቃጥሏል። በዞኑ በኪረሙ ወረዳና አካባቢው የሚገኙ የክልሉ የፀጥታ አካላት መስከረም 26/2014 ዓ.ም አካባቢውን ለቀው መውጣታቸውን ተከትሎ ጥቃቱ ተፈፅሟል። አብዛኞቹ ቀበሌዎች ውስጥ የመንግስት ፀጥታ አካላት ባለመኖራቸው አሁንም የፀጥታ ስጋት መኖሩን ነው ነዋሪዎቹ የተናገሩት።

በዞኑ የሃሮ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑትና በፀጥታ ችግሩ ምክንያት ስማቸውን መናገር ያልፈለጉ አስተያየት ሰጪ እንደተናገሩት በአካባቢው በተከፈተው ጥቃት ሀብት ንብረታቸው ማጣታቸውን ተናግረዋል። በአካባቢው በተፈጠረው ችግር ቀዬያቸውን ለቀው ወደሌላ አካባቢ ሸሽተው እንደሚገኙም ገልጸዋል።

እንደ ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘገባ እስከ አሁን ድረስም የመንግስት አካልም ሆነ የፀጥታ አካላት በአካባቢው ባለመግባታቸውና ባለመቆጣጠራቸው ምክንያት በተፈጠረው አለመረጋጋት የሞቱ ሰዎችን አስክሬን አንስቶ መቅበር አለመቻሉንም አመልክተዋል።