
የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማህበራዊና የልማት ኮሚሽን በዎላይታ ዞን በአምስት ወረዳዎች ተግባራዊ የሚሆን ከ29 ሚሊዮን ብር በላይ ፕሮጀክት ይፋ አደረገ።
ፕሮጀክቱ በዞኑ ከ450 ሺህ በላይ ሰዎችን በቀጥታና በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን በዛሬው ዕለት የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ይፋ ሆኗል።
የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማህበራዊና የልማት ኮሚሽን የዎላይታ ሶዶ ማስተባበሪያ ቅርንጫፍ ኃላፊ አቶ ሙሉነህ ተስፋዬ ፕሮግራሙን ይፋ በሚደረግበት ወቅት እንደገለፁት ስራው በዞኑ ውስጥ የግብርና ዘሮችን በአምስት ወረዳዎች ውስጥ ለሚገኙ ለተመረጡ ተጠቃሚወች ለማድረስ የታለመ መሆኑን አስረድተዋል።

ፕሮጀክቱ ለአንድ አመት የሚቆይ ሲሆን በዞኑ በክንዶ ኮይሻ፣ ዱጉና ፋንጎ፣ ሆብቻ፣ ቦሎሶ ቦምቤና ዳሞት ወይዴ ወረዳዎች ውስጥ በተመረጡ አርባ ቀበሌዎች ተግባራዊ እንደሚሆን አቶ መሉነህ ተናግረዋል።
ለተግባራዊነቱ 29,347,874.00 ብር ከአሜሪካ ዩሴኤድ እና ሲአርኤስ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ሲሆን በዞኑ የግብርና ምርት ዘር አቅርቦት፣ አትክልት ለሚያመርቱ የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ፣ በዘርፉ ስልጠና በመስጠት ከ75 ሺህ በላይ ሰዎችን በቀጥታና 375 ሺህ በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑንም ኃላፊው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማህበራዊና የልማት ኮሚሽን የዎላይታ ሶዶ ማስተባበሪያ ቅርንጫፍ በደቡብ ክልል አምስት ዞኖችና አራት ልዩ ወረዳዎች ውስጥ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ለህብረተሰቡ ተግባራዊ አድርጎ እየሰራ የሚገኝ ተቋም መሆኑን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።