በደቡብ ክልል በቤንች ሸኮ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ ተከስቶ የነበረውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ባህላዊ የእርቅ ስነ-ስርአት ተካሄደ።
ከአንድ አመት በፊት በአካባቢው በተከሰተው ግጭት ተሳትፈው ወደ ጫካ ገብተው የነበሩ ከ37 በላይ ወጣቶችም ወደ ሰላማዊ ኑሮአቸው ተመልሰዋል።
የአካባቢው ማህበረሰብ ሰላሙን ለመበጥበጥ እና ልማቱን ለማደናቀፍ ተቀናጅተው እየሰሩ ያሉትን የውጭ እና የውስጥ ኃይሎችን ነቅቶ እንዲጠብቅም የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፍቅሬ አማን ጠይቀዋል።
የእለቱ የክብር እንግዳ እና የደቡብ ክልል ርእሰ መስተዳድር ተወካይ አቶ ኩታዬ ኩስዬ በበኩላቸው ሰላም የሚጠበቀው በአገር ሽማግሌ እና በአመራሮች ብቻ ሳይሆን በእያንዳንዱ ዜጋ ተሳትፎ በመሆኑ ሁሉም ሰላሙን ነቅቶ እንዲጠብቅ እና የተጀመረውን ልማት እንዲያስቀጥል ጠይቀዋል።
በግጭቱ የተፈናቀሉ ወገኖችንም በአቃፊነት ስሜት በመርዳት የነበረውን ወንድማዊ ትስስር ማስቀጠል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በጫካ የነበሩት ወጣቶችም በድርጊታቸው መፀፀታቸውን እና ህብረተሰቡን ለመካስ መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።
እንደ ኢቢሲ ዘገባ ባህላዊ መንገድ በተካሄደው የእርቅ ስነ-ስራትም ወጣቶቹ የአገር ሽማግሌዎችን እና የአካባቢው ነዋሪዎችን ይቅርታ በመጠየቅ ተጠናቅቋል።

