
የደቡብ ክልል ምክር ቤት፤ ለአዲሱ 11ኛ ክልል የስልጣን ርክክብ ለማድረግ አስቸኳይ ስብሰባ ጠራ
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ቅዳሜ በሚያካሂደው ስብሰባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ህዝበ ውሳኔ ውጤትን ያጸድቃል ተብሏል።
የደቡብ ክልል ምክር ቤት ለአዲሱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የስልጣን ርክክብ ለማድረግ ለሚቀጥለው ሳምንት ሰኞ ጥቅምት 22፤ 2014 አስቸኳይ ስብሰባ መጥራቱ ተገልጿል።
ከዚህ ስብሰባ አንድ ቀን አስቀድሞ አስቸኳይ ስብሰባውን የሚያካሄደው የፌዴሬሽን ምክር ቤትም፤ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልልን ለመመስረት የተካሄደውን የህዝበ ውሳኔ ውጤት ያጸድቃል ተብሏል።
በደቡብ ክልል ስር የነበሩ አምስት ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ የራሳቸውን የጋራ ክልል ለመመሰረት የሚያስችላቸውን ህዝበ ውሳኔ ያካሄዱት ባለፈው መስከረም 20፤ 2014 ነበር። በዕለቱ ድምጽ ለመስጠት ከወጡ 1,262,679 የአካባቢው ነዋሪዎች መካከል 96 በመቶው የአዲሱን ክልል መመስረት መደገፋቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።
ምርጫ ቦርድ የህዝበ ውሳኔውን ውጤት ለፌደሬሽን ምክር ቤት በደብዳቤ እንዳሳወቀ የምክር ቤቱ ህዝብ ግንኙነትና የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተረፈ በዳዳ ተናግረዋል። ምክር ቤቱ በመጪው ቅዳሜ ጥቅምት 20፤ 2014 በሚያካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የህዝበ ውሳኔውን ውጤት ያጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም አስረድተዋል።
ከዚህ ስብሰባ አንድ ቀን በኋላ በሚደረገው የደቡብ ክልል ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ፤ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል 11ኛው ክልል መሆኑ የሚረጋገጥበት ይሆናል ተብሏል። በዚሁ አስቸኳይ ስብሰባ ላይ የደቡብ ክልል ምክር ቤት ለአዲሱ ክልል የስልጣን የሚያስረክብ መሆኑን የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጮች አስታውቀዋል ሲል ዘግቧል።