በሀገረ ናይጀሪያ ባለፉት እሁድና ቅዳሜ እራሱን ለመሸጥ በማህበራዊ ሚዲያ ሲቀሰቅስ የነበረው ግለሰብ በፖሊስ መያዙ ተሰምቷል፡፡
ራሱን በገንዘብ ለመሸጥ ጨረታ ያቀረበው ግለሰብ በፖሊስ ተያዘ
የሀገሪቱ እስላማዊ ፖሊስ ለቢቢሲ እንዳስታወቀው ከሆነ የ26 አመት እድሜ ያለው አልዩ ኢድሪስ የተባለ ግለሰብ፤ ማህበራዊ ሚዲያን ተጠቅሞ እኔን መግዛት የሚችልና የሚፈልግ ካለ እራሴን ለመሸጥ ዝግጁ ነኝ እያለ ሲቀሰቅስ ነው የያዝነው ብሏል፡፡
ግለሰቡ እራሱን ለመሸጥ ያቀረበው ገንዘብ ደግሞ 20 ሚሊዮን ናይራ ወይም 49 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ነው፡፡
እንደግለሰቡ አባባል ከሆነ ደግሞ እራሱን ለመሸጥ የወሰነው በከባድ ድህነት ውስጥ እንደሚኖር ከገለጸ በኋላ አማራጮችን ብዙ ፈለኩ ነገር ግን ለጊዜው የመጣልኝ ሃሳብ ይሄው ብቻ ነበር ብሏል፡፡
በምትኩ ደግሞ የጠየኩትን ገንዘብ ከፍሎ እኔን ለሚገዛኝ ሰው ሰራተኛው በመሆን አገለግለዋለሁ ሲል ይናገራል ግለሰቡ፡፡
ምናልባት እኔ ለራሴ የገመትኩትን ወይም የጠየኩትን 20 ሚሊዮን ናይራ ዋጋ ከፍሎ የሚገዛኝ ሰው ካገኘሁ፤ 10 ሚሊዮን ናይራ የሚሆነውን ለወላጆቼ እሰጣለሁ፤ 5 ሚሊዮን ናይራ ለመንግስት ግብር እከፍላለሁ፤ 2 ሚሊዮን ናይራ የሚሆነውን ደግሞ እኔን ሊገዛኝ የሚችለውን ሰው ላገናኘኝ ደላላ ወይም ማንኛም ሰው እሰጣለሁ፤ የተቀረውን ግን ለራሴ የኪስ ገንዘብ አደረርገዋለሁ የሚል እቅድ እንደነበረውም ለጋዜጠኞች አንድ በአንድ አስረድቷል፡፡
ነገር ግን የሀገሪቱ እስላማዊ ፖሊስ አንድ ሰብዓዊ ፍጡር እራሱን በገንዘብ ለክቶ ወይም መዝኖ መሸጥም ይሁን መግዛት ፈጽሞ የተከለከለ በመሆኑ ግለሰቡ እንዲያዝ ተደርጓል ብሏል፡፡