ተማሪዎችን በክተት ወደ ትምህርት ገበታ የመመለስ ዘመቻና የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ማጠቃልያ ፈተና የማስፈፀሚያ ዕቅድ ላይ ውይይት ተካሂዷል።

የጌዴኦ ዞን ትምህርት መምሪያ ተማሪዎችን በክተት ወደ ትምህርት ገበታ የመመለስ ዘመቻና የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ማጠቃልያ ፈተና የማስፈፀሚያ ዕቅድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።

በመድረኩም ለ2014 ዓ.ም ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህፃናት ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመጡ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እንዲሰሩና ድጋፋዊ ክትትሉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተብራርቷል።

ከተነሱት ዋና ዋናዎቹ  ሀሳቦች መካከል የትምህርት ጥራት፣ የተማሪዎች መጠነ ማቋረጥና መቅረት፣ ከመምህራን ልማት፣ ከህብረተሰብ ተሳትፎ እና ከቅንጅታዊ አሰራር አኳያ የሚታዩ ውስንነቶች በ2014 የትምህርት ዘመን ትኩረት የሚሰጡ ጉዳዮች እንደሆኑ በስፋት ተነስተው የምክክር መድረክ ተካሂዷል።

የተማረ ዜጋና ማህበረሰብ የተሻለ ሀገር ለመፍጠር ብቸኛ አማራጭ ትምህርት  መሆኑን በስፋት የተነሳ ሲሆን ለዚህም ትኩረት በመስጠትና የትምህርት ጥራት ለማስጠበቅ ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ ቀርቧል።

መድረኩን በምክትል ዋና አስተዳዳሪ ማዕረግ የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዮት ደምሴ፣ የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተወልደ ተስፋዬና የትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዘማች ክፍሌ በጋራ መምራተቸውን የዞኑ ህዝብ ግንኙነትና ሚዲያ ዘርፍ ለዎሊይታ ታይምስ ያደረሰው መረጃ ያመለክታል።