ምክር ቤቱ ከተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት አንዱ የብሔር ብሔረሰቦችን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ወይም ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎች ሕገ-መንግስታዊ እልባት መስጠት ነው።

በዚህ መሰረትም በ2012 ዓ.ም ለምክር ቤቱ ከቀረቡለት ጥያቄዎች መካከል የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ጉዳይ አንዱ እንደሆነ ነው የተገለፀው።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኙ አምስት ዞኖችና አንድ ልዩ ወረዳ ራሳቸውን ችለው በክልልነት ለመደራጀት ሕዝበ ውሳኔ አካሂደዋል።

ለህዝበ ውሳኔው መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም በተካሄደው ድምፅ አሰጣጥ አምስቱ ዞኖች እና አንዱ ልዩ ወረዳ አንድ የጋራ ክልል መመሥረቱን ደግፈው 1 ሚሊዮን 221 ሺህ 92 ድምፅ ሰጥተዋል።

በአንጻሩ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል አካል ሆነው መቀጠልን ደግፈው 24 ሺህ 24 ድምጽ መስጠታቸው ይታወቃል።

በውጤቱ መሠረትም የፌዴሬሽን ምክር ቤት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያን ህዝበ ውሳኔ ውጤት መሰረት አድርጎ በነገው እለት ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ የሕግ አማካሪ ዶክተር ዘለቀ ተመስገን በነገው የምክር ቤቱ ጉባኤ ከተያዙት አራት አጀንዳዎች መካከል አንደኛው የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያን ህዝበ ውሳኔ ምርጫ ተከትሎ ውሳኔ መስጠት መሆኑን ገልጸዋል።

“የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አምስት ዞኖችና አንድ ወረዳ እራሳቸውን ችለው በክልልነት ለመደራጀት በወሰኑት መሰረት ምክር ቤቱ የሚወስን ይሆናል” ብለዋል ዶክተር ዘለቀ።

ምክር ቤቱ 6ኛ የፓርላማ ዘመን 1ኛ ዓመት የስራ ጊዜ 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባውን ነገ ያካሂዳል።

በስብሰባው የቋሚ ኮሚቴዎች ዕቅድና ከዚህ በፊት የነበረውን ቃለ ጉባኤም መርምሮ እንደሚያፀድቅ ይጠበቃል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።