


የኃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን ለደቡብ ኦሞ ሴቶች የገንዘብ ድጋፍ አደረገ
በኃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን በተደረገላቸው የገንዘብ ድጋፍ በማህበር በመደራጀት ለተሻለ የኢኮኖሚ አቅም እንደሚሠሩ በደቡብ ኦሞ ዞን በበናፀማይ ወረዳ የቀይ አፈር ከተማ ሴቶች ገለፁ።
ከዚህ በፊት ምንም ሥራ እንደሌላቸው የሚናገሩት ከኤልሻዳይ ማህበር አባላት መካከል ወ/ሮ የኔሽ ሶሳ እና ሂሩት አልታዬ በኃይለማርያም እና ሮማን ፋውንዴሽን 48 ሺህ ብር ብድር ተመቻችቶላቸው በባልትና ሙያ ዘርፍ 2 ወንድና 6 ሴት በድምሩ 8 ሆነው እየሠሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በቀጣይ ጠንክረው በመሠራት ለተሻለ የኢኮኖሚ አቅም ለመብቃት ተግተው እንደሚሠሩ ገልፀው ምቹ ሁኔታ ለፈጠረላቸው ለኃይለማርያም እና ሮማን ፋውንዴሽን ምስጋና አቅርበዋል።
የፋውንዴሽኑ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬ በስፍራው ተገኝተው ጅምር የሴቶች እንቅስቃሴን የጎበኙ ሲሆን የተደራጁ ሴቶች በርትተው እንዲሰሩና ለሌሎችም አርአያ መሆን እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ወደተሻለ ደረጃ ለመድረስ ከአነስተኛ ቦታ መነሳት ግቡን ለማሳካት እንደሚረዳም እንዲገነዘቡ የገለፁት ወ/ሮ ሮማን የትኛውንም ሥራ ሳይንቁ ራሳቸውን ለመቻል ጠንክረው መሥራት እንዳለባቸውም መክረዋል።
ሴቶቹ በባልትና፣በሻይ ቡናና መሰል የሥራ ዘርፎች ተደራጅተው እየሠሩ እንዳሉ መረዳት ተችሏል።
ፍውንዴሽኑ በአከባቢው የትምህርት ምግበ ፕሮግራም ይፋ ማድረጉም ተገልጿል።