የዎላይታ ዞን ፖሊስ መምሪያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በተመለከተ የጸጥታ መዋቅሩ ከሕዝቡ ጋር ተቀናጅቶ እየሠራ መሆኑን ገልጿል፡፡
የዎላይታ ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኢንስፔክተር ጎኣ ኩሳ እንደተናገሩት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በተመለከተ በሁሉም የዞኑ መዋቅሮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ተሠርቷል፡፡
ፈቃድ ያላቸው መሣሪያ የታጠቁ ግለሰቦችን በሚመለከት የያዙትን መሣሪያ አስመዝግበው መጠቀም እንደሚችሉ ገልጸው ይወረሳል የሚል ስጋት ሊኖርባቸው እንደማይገባ ተናግረዋል፡፡
አዛዡ አክለውም ፈቃድ ያለውን የጦር መሣሪያ የያዙ ግለሰቦች ከዚህ በፊት በሀገራችን ብሎም በክልላችን ከተገለጸው ጊዜ ገደብ ላይ ቅዳሜና እሁድን ሳይጨምር አንድ ሳምንት ተጨማሪ ጊዜ መሰጠቱን ጠቁመው በተገለጸው ጊዜ ገደብ ውስጥ ሁሉም የጦር መሣሪያ የያዘ አካል በማስመዝገብ ህጋዊ እንዲሆን አሳስበዋል፡፡
በሌላ በኩል የግልም ሆነ የመንግስት ባለሁለት እግር ሞቴር ተሸከርካሪዎችን በአቅራቢያቸው በሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ በሁለት ቀናት ዉስጥ ማስመዝገብ እንዳለባቸው አሳስበው ማንኛውም አካል ከተፈቀደለት ጊዜ ዉጪ ሳያስመዘግብ ሲያሽከረክር ቢገኝ በአዋጁ በተቀመጠው መሠረት እርምጃ የሚወሰድ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
አዛዡ ለዞኑ ኅብረተሰብ ባስተላለፉት መልዕክት እያንዳንዱ ግለሰብ ከሰፈሩ ጀምሮ አካባቢውን እንዲጠብቅ፣ ከጸጥታ አካላት ጋር እንዲተባበር እንዲሁም ፀጉረ-ልዉጦች ሲገኙ ለሚመለከተው የጸጥታ አካል ጥቆማ በማድረግ ለጸጥታ ዘብ እንዲቆም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
