በዞኑ የሚገኙ የተለያዩ የሴቶች አደረጃጀት የሀገር ሉዓላዊነትን በማስከበር ላይ ለሚገኘው የሀገር መከላከያ ሠራዊት የስንቅ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑ ተገልጿል።
በዞን ማዕከል የሴቶች አደረጃጀት ከ400 ሺህ ብር በላይ ገቢ በመሰብሰብ ለመከላከያ ሠራዊት በሰንባች ስንቅ እያዘጋጁ መሆናቸውን ታውቋል።
ሰላምን ለማስከበር ተሰማርተው ለሚገኙ የሠራዊት አባላት የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም የጌዴኦ ሴቶች ሊግ የፖለቲካና ረዕዮተ ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ ነፃነት በቀለ ተናግረዋል።
በዞኑ ብልጽግና ፓርቲ የሴቶች ሊግ ከተለያዩ አደረጃጀቶች ጋር በመተባበር እያከናወነ ያለው የስንቅ ዝግጅት ለሠራዊቱ ደጀንነትን ለማሳየት ያለመ እንደሆነ ኃላፊዋ አብራርተዋል።
ኢትዮጵያን ለመበታትን የተነሳውን የአሸባሪ የህወሓት ቡድን ሴራ ለማጥፋት በሚደረገው እንቅስቃሴ ሴቶች የሚጠበቅባቸውን ድርሻ በመወጣት የታሪክ አሻራቸውን አስቀመጠው ማለፍ እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
በስንቅ ዝግጅቱ የተሰማሩ ሴቶች በበኩላቸው በሌሎች ግንባሮች ተሰማርቶ ለሚገኘው ሠራዊት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ለማድረግ ከመቼውም ግዜ በላይ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
በተጨማሪም በወረዳዎችና ከተማ አስተዳደር በዞን የተጀመረው የስንቅ ዝግጅት እንደምቀጥልና ለዚህም ሁሉም በመሳተፍ “እናትነትን” ለሠራዊቱ በተግባር ለማሳየት ሁሉም ሴቶች እንዲረባረቡ ጥሪ መቅረቡን የህዝብ ግንኙነትና ሚዲያ ዘርፍ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ የላከው መረጃ ያመለክታል።

