“ደጀንም፣ ዘማችም በመሆን የሀገራችንን ሕልውና እንታደጋለን” በሚል የደቡብ ክልል ለሀገር መከላከያ ሠራዊት የገንዘብና የዓይነት ድጋፍ እንዲሁም ለምልምል የሠራዊት ዓባላት በቡታ ጅራ ከተማ የሽኝት መርሃ ግብር አካሂዷል፡፡
በሽኝት መርሃ ግብሩ ላይ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳው እንደተናገሩት የክልሉ ሕዝብና መንግስት ከምን ጊዜውም በላይ ሀገርን የማዳን ተልዕኮ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀው፣ በግንባር የሚገኘውን የሀገር መከላከያ ሠራዊት ለመደገፍ ከዚህ ቀደም አራት ጊዜ የገንዘብና የዓይነት ድጋፍ መደረጉንና በዛሬው ዕለትም ከ380 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የዓይነት ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳደሩ አክለው እንደተናገሩትም ከ5100 በላይ ሰንጋዎችና ሙክቶች ድጋፍ የተደረጉ ሲሆን የክልሉ የመንግስት ሰራተኞችም ለመከላከያ ሰራዊቱ ያዘጋጁትን ስንቅ ከምልምል ሠራዊቱ ጋር በአንድ ላይ የሚሸኝ ይሆናልም ብለዋል፡፡
የሀገርን ሕልውና ለማስጠበቅ የክልሉ ሕዝብ ከምን ጊዜውም በላይ አንድነቱን ያሳየበት የሽኝት መርሃ ግብር እንደሆነ የተጠቀሰ ሲሆን ሀገር እስክትረጋጋና ወደ ቀደመ ሠላሟ እስክትመለስ ድረስ በሁሉም ዘርፍ ድጋፉ እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡
በዓለም ዓቀፍ ሚዲያዎች እየተደረገ ባለው ፕሮፖጋንዳና የሀሰት ዜናዎች ኢትዮጵያ ለጠላቶቿ የማትንበረከክ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ከምን ጊዜውም በላይ አንድነትን ማጠንከር እጅግ አስፈላጊ እንደሆነም ተገልጿል፡፡
