በዎላይታ ዞን ካሉት ስድስት የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች አንዱ በዞኑ ድጉና ፋንጎ ወረዳ የሚገኝ የቢጠና የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ነው፡፡ ሆስፒታሉ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ የማህበሰቡን የጤና ችግር ለመቅረፍ እንዲሁም ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ደረጃ የሚገኘውን የኢኮኖሚ ጫና ለመቀነስ ጊዜንና ወጪን ባገናዘበ መልኩ አገልግሎት ከመስጠት ረገድ የበኩሉን የማይተካ ሚና እየተወጣ ነው፡፡
ሆስፒታሉ በህክምና አገልግሎት ሰጪነት ግንባር ቀደም በመሆን እውቅና ከማግኘት አልፎ ልምድ የሚቀሰምበት ተቋም ለመሆን መብቃቱ ይወሳል፡፡ በተለይ ወላድ እናቶች እንክብካቤና ህጻናት ህክምና እስከ ቀዶ ጥገና ህክምና በጥራት ከመስጠት ረገድ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት ነው፡፡ በዚህና በሌሎች የህክምና አገልግሎቶች የህብረተሰቡ መመኪያና ኩራት ስለመሆኑን ብዙዎች ይመሰክራሉ፡፡ እንዲያውም የማያቋርጥ ለውጥ እያሳየ የመጣ ተቋም ነው በማለት ሲያሞካሹት ይደመጣል፡፡
አሁን ግን ይህ ነገር ተቀይሯል ያ። በጎ ተግባሩ አብሮት አይነሳም፡፡ በ”ነበር” ካልሆነ በቀር፡፡ ሆስፒታሉ ቀስ በቀስ ቁልቁል እየወረደ ህልውናውን፣መልካም ስሙን እና ግርማ ሞገሱን፣ ማስቀጠል አቅቶት ዳዴ ማለት የጀምረ ይመስላል፡፡ የቢጠና ሆስፒታል እስካለ የጤና ሥጋት የለም ሲባል የነበረው ሁሉ ታሪክ ብቻ እንዳይሆን ነው ነገሩ፡፡
“ሥነ-ምግባር” በቅርቡ በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ተገኝቶ ምልከታ አድርጓል። አንድ ሰው ገና ከሆስፒታሉ መግቢያ በር ላይ ሲደርስ በውስጡ የሆነ ችግር እንዳለ መገመት አያቅተውም፣ ድባቡ ለየት ያለ ነገር ስለመኖሩን በግላጭ ያሳብቃል፡፡
ለማንኛውም በየህክምና መስጫ ክፍሎች በር ላይ ቁጭ ብለው ወረፋ የሚጠባበቁ ጥቂት ታካሚዎች ይታያሉ፡፡ መድኃኒት ክፍል፣ምርመራ ክፍል፣ ካርድ እና የወሊድ ክትትል አገልግሎት ክፍሎች ታካሚዎች ያሉበት ነው፡፡ የአገልግሎት አሰጣጡ ቀልጣፋና ያልሆነ፣ መጉላላት የሚበዛበት ነው ይላሉ ታካሚዎቹ፡፡ ለዚህም አንዱ ምክንያት፤ብዙ ጊዜ የህክምና ባለሙያዎች በሰዓት ስለማይገቡና ሊቀሩም ስለሚችሉ ነው ሲሉ ይማረራሉ፡፡
አገልግሎት የሚሰጥባቸው ክፍሎች ሁሉ ክፍት ሆነው ግን የሚያስተናግድ ባለሙያ አይታይም፡፡ መውጫ ወረቀት የሚሰጥ የለም፣ የታዘዘ መድሐኒት ማን ይስጥ? ደስ ሲላቸው መጥተው ያስተናግዳሉ፣ ደግሞ ይሄዳሉ፡፡ ወዴት ነው የሚሄዱት ሲባል ከመውጫ በር በስተቀኝ በኩል ባለ ስፍራ በቁጥር ከአምስት የማይበልጡ ግለሰቦች የሞቀ ወሬ ይዞ ከሩቅ ይታያሉ፣ ለካ! የጤና ባለሙያዎች ኖሯል፡፡ በቢጠና ሆስፒታል የህክምና ባለሙያ ከሌላ ሰው መለየት ከባድ ነው፡፡ የጤና ባለሙያዎች መለያ እና ኩራት የሆነው ነጩ ጉዋን እነሱ ጋር ቦታ አላገኘም፡፡
ነገሩ እንዲህ ከሆነማ፣አንዳች ነገር ተፈጥሮ መሆን አለበት የሚል ግምት አለ፡፡ ምን ተፈጥሮ ይሆን ለሚለው ጥያቄ መልስ ለማግኘት ከአንደበታቸው መስማት ግድ ሆኖብን አነጋገረናቸዋል፡፡
የአገልጋይነት ስሜት የገደለ የሞራል ውድቀት ያስከተለ ነው የሚሉት ችግር ስለመፈጠሩን በብሶትና በምሬት ሲገልጹ ይደምጣሉ፡፡ ለዚህ ሁሉ ያበቃቸው አንድ ቁምነገር አለ፡፡ ይህም በ2013 በጀት ዓመት ተቋሙን ሲያገለግሉ በወቅቱ መከፈል የነበረ የ10 ወራት የትርፍ ሰዓት[ duty]፣ማትጊያ [Top up]፣ የአደጋ ተጋላጭነት ክፍያ እና ጥቅማጥቅም እስካሁን አለመከፈሉ ከፍተኛ ቅሬታ እንዳሳደረባቸው ነው የሚያብራሩት ባለሙያዎቹ፡፡
የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደቱ ያለአንዳች እክል የማሳለጥ ሙያዊ ግዴታ እየተወጡ ጎን ለጎን የመብት ጥያቄያቸው ምላሽ እንዲያገኝ ሲሉ ደጅ ያልጠኑበት የመንግስት ተቋም፣ በጽሁፍ እና በአካል ያላሳዉቁበት ባለሥልጣን እንደሌለ አንስተዋል፡፡ በተደጋጋሚ ጊዜ ለወረዳውና እና ለዞን መንግስት አቤት ቢሉ ዛሬ ነገ እየተባለ ከፊታቸው ለመሸኘት ብቻ በውሸት ሲያታልሉ ኖረዋል፡፡ ቅሬታቸውን ማቅረብ ከጀመሩ አንድ ዓመት ሊሞላ ሁለት ወር ቀርቶታል ሲሉ ተስፋ በቆረጠ አንደበት ይናገራሉ፡፡
በአንድ ወቅት ሥራ የማቆም አድማ ሁሉ አድርገው፣ የተወሰኑ ሐክሞች ለእስራት ተዳርገው ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ትኩረት ተነፍጎ የከረመ ጥያቄያቸው እንዲዳፈን የሚያደርግ ከመሆኑ አልፎ ተጨማሪ የሞራል ጉዳት ያስከተለ፣የሥራ ተነሳሽነት የቀበረ እንደሆነባቸው ይናገራሉ ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን በሆስፒታሉ ውስጥ ብዙዎችን ያስቆጣና ያሳዘነ የሥነ-ምግባር ጥሰት መፈጸሙን ሰምተናል፡፡
የጤና ባለሙያዎቹ የሚያነሱት ቅሬታ ከተገቢነት አንጻር ለድርድር የሚቀርብ ባይሆንም ጥያቄያቸው ለማሰማት የተካሄደ ርቀት እና የተወሰደ እርምጃ ሙያውን የማይመጥን ድርጊት ከመሆኑ በላይ ሰብአዊነት የጎደለው ነው፡፡ ህክምና ፈልጎ የመጣን ታካሚ፣ “ሂድ እዚያ አስተዳደር ጋር ሄደ ታከም” ከማለት በዘለለ ታካሚው ላይ የተደቀነ ጉሎኮስ በመንቀል ከሆስፒታሉ እስከማባረር መድረስ ግን የሥነ-ምግባርን ዝቅጠትን ደረጃ ያሳያል። በዚህ መልክ የመብት ጥያቄ ለማቅረብ መሞከር እጅግ ያስነውራል፡፡ ያስደነግጣልም፡፡
የዜጎች ህክምና አገልግሎት የማግኘት መብት በመርገጥ ርህራሄ እና ሰብአዊነት የጎደለው እኩይ ድርጊት መፈጸም በምንም ሚዛን ተገቢ ሊሆን አይችልም፡፡
ተመስገን ሉቃስ (ዶ/ር) በሆስፒታሉ የሜዲካል ዳይሬክተር፣በአሁን ወቅት ሆስፒታሉ መሰረታዊ የህክምና አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል ቢሉም በቂና የተሟላ ነው ለማለት አይደፍሩም፡፡ ሆስፒታሉ ከብዙ ችግሮች ጋር እየታገለ ይሰራ የነበረው ውጤታማ ሥራ ከአንድ ዓመት ወዲህ አጠቃላይ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ችግር ተፈጥሯል ይላሉ፡፡
ባለሙያዎቹ የሚያነሱት ጥያቄ ከበጀት ጋር የሚያያዝ ነው፣ ይህ ደግሞ ከሆስፒታሉ አቅም በላይ ነው፡፡ ለጥያቄያቸው ተገቢ ምላሽ እንዲገኝ የተደረገ ያልተቋረጠ ጥረትና ትግል ፍሬያማ እንዳልነበረም ያነሳሉ ዳይሬክተሩ፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር እና የሥነ-ምግባር ግድፈት ፈር ለማስያዝ እንዳልተቻለ እንዲሁ፡፡
ለምን? የህክምና ሥራ ከየትኛው ሙያ በላይ በቡድን የሚከናወን ነው፣ ከቡድኑ የአንዱ ባለሙያ ሞራል ከተነካ፣ ስሜቱ ከተረበሸ ህክምናው ውጤታማና የተሳካ የመሆን ዕድሉ ዝቅተኛ ሲሉ ያትታሉ፡፡ እሳቸው የተለያዩ ምክንያቶች በመደርደር ተቋሙ የጤና ተቋም መሆኑን የዘነጉ ይመስል የዘቀጠውን የሥነ-ምግባር ግድፈትና ቅጥ ያጣ የአገልግሎት አሠጣጥ ችግር ለመፍታት በዝምታ ከማለፍ ውጭ ሌላ መፍትሔ የሚያፈላልጉ አይመስልም፡፡
ባለሙያው አርፍዶ ሲገባ ይሁን ቀድሞ ሲወጣ ዝም ይባልና ክፍተት ሲፈጠር ተክቶ ለመስራት መሯሯጥ ወንዝ የሚያሻግር አይደለም፡፡ ግራ ነፈሰ ቀኝ፣ በዚህ መሃል ከማንም በላይ የሚጎዳው ደሃው የህብረተሰብ ክፍላችን ነው፡፡ አሁንም ህመምንተኛው ሩቅ አካባቢ እንዲለፋ ሲፈረድበት ቸልተኛው የቢጠና ሆስፒታል ግን ሊታደጋቸው አልቻለም፡፡
የወረዳው አስተዳደር መዋቅርስ?
አቶ አሰፋ ሻንቆ በዎላይታ ዞን የድጉና ፋንጎ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ ናቸው፡፡ ወረዳቸው ከአቅም በላይ የሆነ የጥሬ ገንዘብ እጥረት በመከሰቱ ከደመወዝ ውጭ ያሉ ማናቸው ክፍያዎች ለመክፈል ተቸግሯል፤ ከዚህ የተነሳ ለወራት ሳይከፈል ይዘገያል፡፡ መስተዳድሩ መክፈል ያቃተው የጤና ባለሙያዎቹ ብቻ ሳይሆን ከመምህራን ጀምሮ በወረዳው የሚገኙ የሌሎች ሠራተኞች ደረጃ ዕድገት፣የትርፍ ሰዓት እና ሌሎች ክፍያዎች ጭምር መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
እንደ አቶ አሰፋ ገለፃ፣የጤና ባለሙያዎቹ ክፍያ በቅድሚያ ሊከፈል እንደሚገባ የወረዳው አስተዳደር በፅኑ ያምናል፡፡በዚህ ጉዳይ ከባለሙያዎቹ ጋር በሰፊ ተወያይተው ችግሩ እስከሚቀረፍ ምንም ዓይነት የሥራ ክፍተት ሊፈጠር እንደማይገባ ተግባብተው እንደነበር ነው፡፡
ነገር ግን ባለሙያዎቹ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚፈፅሙት ያልተገባ ኢ-ሥነ-ምግባራዊ ድርጊት ተገቢነት የለውም ይላሉ፡፡ አይደለም የጤና ባለሙያ በየትኛው የሥራ መስክ የተሰማራ ሠራተኛ ከምን በላይ የሰውን ሰብአዊ ክብር የመጠበቅ ሞራል ማጣት የለበትም፡፡ የሙያ ሥነ-ምግባር ቢጎደል የህሊና ሥነ-ምግባር ሙሉ ይሆናልና ሁሌም ነገሮችን በጽሞና ማየትና ትዕግስተኛ መሆን ሩቅ ለመጓዝ ስንቅ ይሆናል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
የሆነው ሆኖ ግን ችግሩን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመቅረፍ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው ያሉት ምክትል አስተዳዳሪው፣ገንዘብ በተገኘ አጋጣሚ ሁሉ የአንድ ወር ይሁን የሁለት ወር እየተፈከለ ውዝፍ ክፍያቸው ይጠናቀቃል፣ በቂ ገንዘብ ከተገኘ ግን በአንዴ እንደሚፈጸምላቸው ቃል ገብተዋል፡፡ የተገባው ቃል በተግባር ሊገለፅ ይገባል፡፡
አሁን ላይ በሆስፒታሉ የሚታየው የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር እና የሥነ ምግባር ዝቅጠት አፋጣኝ እልባት የሚሻ ነው፡፡ ከደቡብ ክልል ሥነ-ምግባር ኮሚሽን

