የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ግንባታ የመጀመሪያ ዙር ኃይል ማመንጨት በሚያስችል ደረጃ እየተገባደደ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ገለፁ፡፡
ግድቡ ተጠናቆ ለታለመለት ዓላማ እንዳይውል የሚሹ የውጭ ኃይሎች ተላላኪያቸው የሆነውን አሸባሪው ትሕነግ በመጠቀም ለማደናቀፍ ቢጥሩም በመላው ኢትዮጵያዊያን ቁርጠኝነት የታላቁ ኅዳሴ ግድብ ግንባታ ወደ መጠናቀቁ ምዕራፍ እየሄደ መሆኑን አሳውቀዋል፡፡
በኢትዮጵያ ላይ እየደረሰ ያለው ጫና መላው ኢትዮጵዊያንን ቁጭት ውስጥ የከተተ ነው ያሉት ሚኒስትሩ ሀብታሙ (ዶ/ር) የኅዳሴ ግድቡ ግንባታ ላይ የሚሰሩ ኢትዮጵያዊያንም በአስቸጋሪ የአየር ሁኔታ ውስጥ ሆነው በከፍተኛ ወኔና በቁጭት 24 ሰዓት እየሰሩ ነው ብለዋል፡፡
ጠላትን ማሸነፍ የሚቻለው በጦር ግንባር ብቻ አይደለም ያሉት ሚኒስትሩ የልማት ሥራዎችን በተገቢው መንገድ በማጠናቀቅና የአገሪቱን ብልጽግና በማረጋገጥ ድልን መጎናፀፍ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ሚኒስትሩ ከዋልታ ጋር ባደረጉት ቆይታ መላው ኢትዮጵያዊያን ለግድቡ ግንባታ የሚችሉትን ሁሉ ድጋፍ እያደረጉ ነው ያሉም ሲሆን አሁንም የሚደረገውን ድጋፍ በማጠናከር ግድቡ ተጠናቆ የሚሰጠውን የኃይል ጥቅም መቋደስ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
