በደቡብ አውስትራሊያ አዴላይድ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የ’#በቃ’ ‘#NoMore’ ሰላማዊ ሰልፍ በዛሬው ዕለት አካሂደዋል።
ሰልፈኞቹ በመልዕክታቸው አሸባሪው ህወሓትና ተላላኪዎቹ ያደረሱትን ዘረፋ፣ ውድመት፣ አስገድዶ መድፈርና የሰላማዊ ሰዎች ጅምላ ግድያን አውግዘዋል።
አንዳንድ ምዕራባውያን መንግስታት በተለይም አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ እያደረጉ ያለውን ያልተገባ ጫና እንዲያቆሙ ጠይቀዋል፡፡
አንዳንድ የውጭ ሚዲያዎችም የሚያሰራጩትን አድሏዊና የተዛባ መረጃ ማሰራጨት እንዲያቆሙ ነው ሰልፈኞቹ የጠየቁት።
ኢትዮጵያ የተመረጠ መንግስት ያላት ሃገር በመሆኗ መንግስትን የመቀየር ስልጣን የኢትዮጵያ ሕዝብ እንጂ በኃያላን ሴራ የሚፈጸም እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡
መንግሥት የኢትዮጵያን አንድነት ለማስጠበቅ በሚያደርገው ጥረት ሁሉ ድጋፋቸው እንደማይለይ እና በተከሰተው ችግር ሰለባ ለሆኑ ወገኖችም በተለያየ መንገድ አጋርነታቸውን እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
ሰልፉን ያስተባበረው የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ማኅበር በደቡብ አውስትራልያ በተያዘው ሳምንት መጨረሻም በሜልቦርን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተመሳሳይ ትዕይንተ ህዝብ እንደሚያካሂዱ መግለጹን ከዳስያፖራ ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
