በኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም የዎላይታ ሶዶ ዲስትሪክት ባለፉት ስድስት ወራት ከግማሽ ቢለዮን ብር በላይ ማሰባሰቡን ገለፀ::

ዲስትሪክቱ የ2014 ዓ.ም የስድስት ወር አፈፃፀም ግምገማ በዎላይታ ሶዶ ከተማ ጉታራ አዳራሽ በዛሬው ዕለት አካሂዷል፡፡

በኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም የሶዶ ዲስትሪክት ሥራ አሥኪያጅ አቶ ተመስገን ያይና በቁጠባ አሰባሰብ፣ በብድር ስርጭትና በብድር አመላለስ ከዕቅድ በላይ መፈፀሙንና ውዝፍ ዕዳ ከማስመለስ ጋር ተያይዞ የሚታየውን ክፍተት ለማረምም በርካታ ቅንጅታዊ ሥራዎች መፈፀማቸውንና ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

በ2014 በጀት አመት በመጀመሪያ ስድስት ወር አፈፃፀም ከ569 ሚሊዮን በላይ ብር አጠቃላይ ቁጠባ ከተለያዩ ደንበኞች ማሰባሰብ መቻሉን ገልፀዋል፡፡

በብድር ስርጭት 139 ሚሊዮን ብር በላይ እና በብድር አመላለስ 144 ሚሊዮን ብር በላይ ማሳካት መቻሉንም አብራርተዋል፡፡

ተቋሙ ወደባንክ ደረጃ የሚያድግ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለደንበኞቹ ሰፊ አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀቱን የጠቆሙት አቶ ተመስገን ሁሉም የተቋሙ አመራሮችና ባለሙያዎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የጀመሩትን ቅንጅታዊ አሰራር አጠናክሮ እንዲቀጥሉና የሚመለከታቸው አካላትም አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የዲስትሪክቱ ደንበኞች ቁጠባን ባህል እንዲያደርጉና የተበደሩትን ገንዘብ በገቡት ውል መሰረት በጊዜ በመመለስ የራሳቸውን ዕድገት እና የተቋሙን ራዕይ ዕውን ለማድረግ በዓላማ መስራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአጠቃላይ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ በብድር የተወሰደው በደምበኞች እጅ መኖሩን በመግለፅ ተጠቃሚዎቹ ገንዘቡን ለአላማ እንደወሰዱት ሁሉ በጊዜ መመለስ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

አቶ መተኪያ ዳካ በዲስትሪክቱ የዳሞታ ኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሥራ አስኪያጅ፣ አቶ ፍቅሬ አጫ የአረካ ከተማ ኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሥራ አስኪያጅ እና አቶ ገዛኸኝ መጃ የዳሞት ጋለ ወረዳ ማይክሮ ፋይናንስ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሥራ አስኪያጅ እንደገለጹት በ2014 በጀት ዓመት በ6 ወር አፈፃፀም በቁጠባ አሰባሰብ፣ በብድር ሥርጭትና ብድር አመላለስ ከዕቅድ በላይ የፈጸሙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በፕሮግራም ከሚሰራጭ ብድር ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር ለመቅረፍ በተሰራው ቅንጅታዊ አሰራር የተሸለ ውጤት መመዝገቡን የጠቆሙት ሥራ አስኪያጆች በዓመቱ በቀረው ጊዜም የተሸለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ  መዘጋታቸውንም አረጋግጠዋል።