የተጠናቀቁት ፕሮጀክቶች በአጠቃላይ ከ200 ሺህ የሚበልጡ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ ተጠቁሟል።

በዩኒቨርሲቲው ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ጽ/ቤት ከ2013 በጀት ዓመት የተሸጋገሩ እና በ2014 በጀት ዓመት ጸድቀው ወደ ስራ ከገቡ የማህበረሰብ አገልግሎትና ተሳሳትፎ ፕሮጀክቶች ውስጥ ባለፉት 6 ወራት ተሰርተው የተጠናቀቁ 8 ፕሮጀክቶች በትላንትናው እለት ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።

በፕሮጀክቶቹ የምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ የተገኙት የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር መስፍን ቢቢሶ፤ ዩኒቨርሲቲው ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር በማድረግና የቅድምያ ቅድምያ ሊሰጣቸው የሚችሉ ፕሮጀክቶችን በመለየት ማኀበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱንና፥ አሁንም እያከናወነ መሆኑን አሳውቀዋል።

በ2014 በጀት ዓመት ከ 300 መቶ ሺህ ህዝብ በላይ ተጠቃሚ የሚያደርጉ 54 ፕሮጀክቶችን በማኀበረሰብ አገልግሎትና ተሳትፎ ዘርፍ ተግባራዊ ለማድረግ በማቀድ ወደ ስራ መገባቱንም ዶ/ር መስፍን ጠቁመዋል።

ፕሮጀክቶቹ ቴክኖሎጂ ላይ የሚያተኩሩ እና የሕዝብን ችግር በዘላቂነት የሚፈቱ እንዲሆኑ የማህበረሰቡን ፍላጎት መሰረት ባደረገ መልኩ ተግባራዊ እንደሚደረግም ምክትል ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ደኣ በበኩላቸው ከመደበኛ ትምህርት ባሻገር ዩኒቨርሲቲው ጥልቅ ሳይንሳዊ ጥናትና ምርምር በማድረግ የአካባቢውን ማህበረሰብ ችግር ለመቅረፍ እየሰራ ያለው ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር የማህበረሰቡን ሕይወት ለመለወጥ ምሁራን የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ፥ ሀብት በማፈላለግ ጭምር የተጀመሩ የማህበረሰብ አገልግሎትና ተሳትፎ ስራዎች በቁርጠኝናት ሊሳተፉ ይገባል ሲሉ ዶ/ር ሙላቱ ገልጸዋል ።

በፕሮጀክቶቹ ምረቃ ላይ የዎላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ተወካይ የሆኑት አቶ ተመስገን ታደሰ የተገኙ ሲሆን፤ ዩኒቨርሲቲው ከመደበኛ የመማር ማስተማር ስራ በተጓዳኝ ጥናትና ምርምር በማድረግ የአካባቢውን ማኅብረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የፕሮጀክቶችን በመተግበር ማህበራዊ ሐላፊኑቱን በሚገባ እየተወጣ ነው ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ በማድረጉ ስራዎችን በመስራቱ የዞኑ አስተዳደር ከፍተኛ ዕውቅና የሰጠ መሆኑን አቶ ተመስገን ተናግረው፤ የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች በአግባቡ በመጠቀምና በመንከባከብ ጥበቃ ሊያደደርጉ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በትላንትናው ዕለት ተመርቀው በይፋ አገልግሎት መስጠት ከጀመሩ ፕሮጀክቶች ውስጥ በቴክኖሎጂ መስክ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰራና የአካል ጉዳተኞችን ችግር የሚፈታ ባለ ሶስት ጎማ ዊልቸር እንዲሁም ባለሁለት ጎን የእህል መፍጫ ማሽን በመስክ ምልከታ ተቃኝቶና ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።

በዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮጀክት እና በሕዝብ ተሳትፎ በመሰረተ ልማት ዝርጋታና መልሶ ማቋቋም ረገድ በዳሞት ወይዴ ወረዳ በዴሳ ከተማ የድልድይ ሥራና በጋልቻ ሳኬ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ሁለት ብሎክ ያላቸው የቤተመፃህፍትና የላቦራቶሪ ህንፃዎች፤ በዳሞት ፑላሳ ወረዳ የድልድይ ግንባታ እንዲሁም በሶዶ ዙሪያ ወረዳ ሾላ ቦርኮሼ ቀበሌ 6 ሺህ ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የኮቴ ገነት የውሃ ፕሮጀክት መልሶ ማቋቋም ተመርቀው ለአገልግሎት መብቃታቸው ተገልጿል።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የዩኒቨርሰቲው ማኔጅመንት አባላት፣ የዩኮሌጅና ትምህርት ቤት ምክትል ዲኖች፣ ባለሙያዎች፣ የዎላይታ ዞን ከፍተኛ አመራሮች የወረዳ አስተባባሪዎች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል ሲል የዩንቨርስቲው ኮሙኒኬሽን ዳይሮክቶሬት ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

%d bloggers like this: