ወጣቱ ትውልድ ባለፉት 27 ዓመታት ከተዘራበት ከብሄርተኝነትና ከጥላቻ አስተሳሰብ ወጥቶ ፍቅርና ሰላምን ሰባኪ እንዲሆን መስራት ይገባል ሲሉ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር አያና በራሶ ተናግረዋል።
የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አባላት ላለፉት 12 ወራት ሲያካሂዱት የነበረው “ትውልድና ጥላቻን የማጣላት ዘመቻ” ንቅናቄ 1ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ትላንት ተከብሯል፡፡
በንቅናቄው የተጻፈ “የጥላቻ ሰንሰለት” የተሰኘ መጽሀፍ ተመርቋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር አያና በራሶ በወቅቱ እንደገለጹት ሃገር በፈተና ውስጥ በገባችበት በዚህ ወቅት የዩኒቨርሲቲው ምሁራን ከመማር ማስተማሩ ጎን ለጎን ችሎታቸውን ተጠቅመው ሰላም ላይ ባተኮረ የማህበረሰብ አገልግሎቶች ላይ መሳተፋቸውን አድንቀዋል፡፡
“ትውልድና ጥላቻን የማጣላት ዘመቻ” ንቅናቄ በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት ተጀምሮ ፍቅርንና አንድነትን በመስበክ ሃገር ለማዳን የሚያደርገው ተግባር ለዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎት ስራ አርአያ የሚሆን ነው” ብለዋል፡፡
ህብረ ብሄራዊ አንድነትን መሰረት ያደረገ ሃገርን የመገንባት ሂደት ስኬታማ እንዲሆን የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጥላቻን ማስወገድ የሚያስችሉ ተግባራት ማከናወን ይገባቸዋል” ሲሉ ፕሬዝዳንቱ አስገንዝበዋል።
በተለይም ወጣቱ ትውልድ ባለፉት 27 ዓመታት ከተዘራበት ከብሄርተኝነትና ከጥላቻ አስተሳሰብ ወጥቶ ፍቅርና ሰላምን መስበክ ላይ እንዲሰማራ ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
“አሁን ባለው አካሄድ ያተረፍነው የለም” ያሉት ፕሬዝዳንቱ አስተሳሰባችንን በመቀየር ከአባቶቻችን የወረስነውን አካታች የሆነ ተከባብሮ የመኖር ባህል ለማሳደግ የጥላቻ ሰንሰለት መበጠስ ያስፈልጋል” ሲሉ ፕሬዝዳንቱ አክለዋል፡፡
“እንደሃገር የገጠመን ፈተና መንስኤው የጥላቻ ውጤት ነው” ያሉት ደግሞ የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ልዩ አማካሪ አቶ ሰሪሚሶ ሳሙኤል መናገራቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።