
ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ ቦሌ ድልድይ አከባቢ ረፋድ ላይ በደረሰ የመኪና አደጋ የሁለት ሰዎች ህይወት አለፈ፡፡
አደጋዉ የደረሰዉ በሲኖ ትራክ እና የቤት መኪና መሃል በተፈጠረ ግጭት ሲሆን ፣ መብራት ይዞት ቆሞ የነበረ የቤት መኪና ላይ ከፍጥነት ገደብ በላይ እያሽከረከረ የነበረ ሲኖ ትራክ መብራት ጥሶ በማለፍ መኪናዉን ገጭቶ አደጋው እንደደረሰ የቦሌ ክፍለከተማ ቡድን መሪ ዋና ሳጅን ወንድሙ አሻግሬ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ገልጸዋል፡፡
በዚህም በቤት መኪናዉ ዉስጥ ከነበሩ 4 ሰዎች መካከል ሁለቱ በዕድሜ ገፋ ያሉ ወንድ እና ሴት ወዲያዉ ህይወታቸዉ ሲያልፍ ፣ ሹፌሩ እና ከጀርባ የነበረች ሌላ ሴት ደግሞ ወደ ህክምና መወሰዳቸውን ዋና ሳጅን ወንድሙ ተናግረዋል፡፡
ዋና ሳጅን ወንድሙ አሻግሬ ለኢትዮ ኤፍኤም እንደገለጹት በመኪናዉ ዉስጥ ከነበሩት 4 ሰዎች መካከል ሹፌሩን ጨምሮ ሶስቱ የአንድ ቤተሰብ አባል እናት፣ አክስት እና ልጅ ሲሆኑ ሌላዉ አንድ ግለሰብ ግን ያለዉ ዝምድና እየተጣራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ዋና ሳጅኑ እንደገለጹት በመብራት ዙሪያ ያለ ሁኔታን በጣም በጥንቃቄ መተግበር እንዳለበት እና መብራት ጥሶ ማለፍ ለብዙ ጉዳቶች የሚያጋልጥ በመሆኑ ሁሉም አሽከርካሪ በጥንቃቄ እንዲያሽከረክር መልዕክታቸዉን አስተላልፈዋል፡፡
