የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በዎላይታ ዞን ቦሎሶ ሶሬ ወርዳ ለሚገኘው ለወይቦ ወጋ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያስገነባውን ዘመናዊ የመማሪያ ህንፃ፣ ወንበርና ጠረጰዛ አስረከበ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ሥራ በተጨማሪ በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርናና በተለያዩ ዘርፎች የአካባቢውን ማህበረሰብ ችግር የሚፈቱ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡

ከሰሞኑ በዩኒቨርሲቲው ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ድጋፍ በተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ በኩል በዎላይታ ዞን ቦሎሶ ሶሬ ወረዳ ወይቦ ወጋ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተሰራ ባለ አራት ክፍል ዘመናዊ ህንጻ ለመማር ማስተማር ሥራ ዝግጁ ሆኖ ለትምህርት ቤቱ ተበረክቷል፡፡

በመማሪያ ክፍሎቹ ወንበርና ጠርጰዛ ተሟልተው ከዩኒቨርሲቲው የሚመለከታቸው አካላት፣ የወረዳ አመራሮች እና የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ አባላት ባሉበት ርክክብ ተደርጓል፡፡

በርክክብ ሥነ-ሥርዓት ላይ የዩኒቨርሲቲው ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑት ዶ/ር መስፍን ቢቢሶ በዞኑ የቅድምያ ቅድምያ የሚሰጣቸውን ችግሮች በመለየት እና ችግሮቹን በሳይንሳዊ መንገድ ለመፍታት ታቅዶ እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።

ዶ/ር መስፍን አክለውም፤ ዩኒቨርሲቲው በ2014 የትምህርት ዘመን ከሦስት መቶ ሺህ በላይ ማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ ተግባራዊ እያደረገ እንደሆነ ተናግረዋል።

በዎላይታ ዞን በወይቦ ወጋ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተደረገው የመማሪያ ክፍልና የትምህርት ሥራ ድጋፎች ዞኑ እየተገበረ ያለውን የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ አይነተኛ ሚና እንደሚጫወት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ገልፀዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የተፈጥሮ ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ዲን የሆኑት መ/ር አሸናፍ አበበ፤ የወይቦ ወጋ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከዚህ በፍት ለመምህራን የሳይንስ ፣ የሂሳብ እና የቤተ-ሙከራ ስልጠና የሰጠ ሲሆን በቀጣይም ለመማር ማስተማር ሥራ አጋዥ የሆኑ ሙያዊ ድጋፎች በተቀናጀ መልኩ ለማስቀጠል ኮሌጁ በትኩረት እየሰራ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲው በቦሎሶ ሶሬ ወረዳ ወይቦ ወጋ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ተቀብሎ እያስተማረ ቢሆንም በት/ቤቱ የተገነባው ህንጻው ለአገልግሎት መብቃቱ በክፍል እጥረት የሚፈጠረውን ችግር የሚቀርፍ ነው ሲሉ የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ አካላት ተናግረዋል፡፡

በትምህርት ቤቱ ከዚህ በፊት የመማሪያ ክፍል ጥምርታ አንድ ክፍል ለሰማንያ ተማሪዎች የነበረው ህንፃው ተጠናቅቆ ሥራ ሲጀምር የመማሪያ ክፍል ጥምርታ አንድ ክፍል ለአርባ አምስት እንዲሆን እንዳደረገ ከትምህርት ቤቱ የተገኘ መረጃ ያመላክታል ሲል የዩንቨርስቲው ኮሙኒኬሽን ዘግቧል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

%d bloggers like this: